Zephaniah 3:14-20

የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፤ እልል በዪ፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፤ በፍጹም ልብሽ ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ። እግዚአብሔር ቅጣትሽን አስወግዶታል፤ ጠላቶችሽን ከአንቺ መልሷል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነው፤ ከእንግዲህ ወዲያ አንዳች ክፉ ነገር አትፈሪም። በዚያ ቀን ኢየሩሳሌምን እንዲህ ይሏታል፤ “ጽዮን ሆይ፤ አትፍሪ፤ እጆችሽም አይዛሉ። እግዚአብሔር አምላክሽ በመካከልሽ አለ፤ እርሱ ብርቱ ታዳጊ ነው፤ በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤ በዝማሬም በአንቺ ላይ ከብሮ ደስ ይሰኛል።” “ስለ ክብረ በዓላት መተጓጐል የተከዝሽበትን፣ የስድብሽን ሸክም፤ ከአንቺ አስወግዳለሁ። በዚያ ጊዜ፣ ያስጨነቁሽን ሁሉ እቀጣለሁ፤ ዐንካሶችን እታደጋለሁ፤ የተበተኑትንም እሰበስባለሁ፤ በተዋረዱበት ምድር ሁሉ፣ ለውዳሴና ለክብር አደርጋቸዋለሁ። በዚያ ጊዜ እሰበስባችኋለሁ፤ ያን ጊዜ ወደ አገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ ዐይናችሁ እያየ፣ ምርኳችሁን በምመልስበት ጊዜ፣ መከበርንና መወደስን፣ በምድር ሕዝብ ሁሉ መካከል እሰጣችኋለሁ”፤ ይላል እግዚአብሔር።
ሶፎንያስ 3:14-20