Psalms 95:1-11

ኑ፤ ደስ እያለን ለእግዚአብሔር እንዘምር፤ በድነታችንም ዐለት እልል እንበል። ምስጋና ይዘን ፊቱ እንቅረብ፤ በዝማሬም እናወድሰው። እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ታላቅ ንጉሥ ነው። የምድር ጥልቆች በእጁ ናቸው፤ የተራራ ጫፎችም የርሱ ናቸው። እርሱ ፈጥሯታልና ባሕር የርሱ ናት፤ እጁም የብስን አበጀ። ኑ፤ እናምልከው፤ እንስገድለትም፤ በፈጣሪያችን በእግዚአብሔር ፊት እንንበርከክ፤ እርሱ አምላካችን ነውና፤ እኛም በእጁ ጥበቃ ሥር ያለን በጎቹ፣ የመሰማሪያውም ሕዝብ ነን። ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣ በምድረ በዳ በነበራችሁበት ቀን በማሳህ፣ በመሪባም እንዳደረጋችሁት፣ ልባችሁን አታደንድኑ። ሥራዬን ቢያዩም፣ አባቶቻችሁ በዚያ ፈተኑኝ፤ ተፈታተኑኝም። ያን ትውልድ አርባ ዓመት ሙሉ ተቈጣሁት፤ እኔም፣ “በልቡ የሳተ ሕዝብ ነው፤ መንገዴንም አላወቀም” አልሁ። ስለዚህ እንዲህ ብዬ በቍጣዬ ማልሁ፣ “ፈጽሞ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም።”
መዝሙር 95:1-11