Psalm 46:1-7

አምላካችን መጠጊያችንና ኀይላችን፣ በሚደርስብን መከራ ሁሉ የቅርብ ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ እንኳ፣ ተራሮችም ወደ ባሕር ጥልቅ ቢሰምጡ አንፈራም። ውሆች ቢያስገመግሙ፣ ዐረፋ ቢደፍቁም፣ ተራሮችም ከውሆቹ ሙላት የተነሣ ቢንቀጠቀጡም አንደናገጥም። ሴላ የእግዚአብሔርን ከተማ፣ የልዑልን የተቀደሰ ማደሪያ ደስ የሚያሰኙ የወንዝ ፈሳሾች አሉ። እግዚአብሔር በመካከሏ ነው፤ አትናወጥም፤ አምላክ በማለዳ ይረዳታል። ሕዝቦች በዐመፅ ተነሡ፤ መንግሥታትም ወደቁ፤ ድምፁን ከፍ አድርጎ አሰማ፤ ምድርም ቀለጠች። የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ነው፤ የያዕቆብም አምላክ መጠጊያችን ነው። ሴላ
መዝሙር 46:1-7