Psalms 24:1-10

ምድርና በርሷ ያለው ሁሉ፣ ዓለምና በውስጧ የሚኖር ሁሉ የእግዚአብሔር ነው፤ እርሱ በባሕሮች ላይ መሥርቷታልና፤ በውሆችም ላይ አጽንቷታል። ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ሊወጣ ይችላል? በተቀደሰ ስፍራውስ ማን ይቆማል? ንጹሕ እጅና ቅን ልብ ያለው፤ ነፍሱን ለሐሰት ነገር የማያስገዛ፤ በውሸት የማይምል። እርሱ በረከትን ከእግዚአብሔር ዘንድ፣ ጽድቅንም ከአዳኝ አምላኩ ይቀበላል። እርሱን የሚፈልግ ትውልድ እንዲህ ነው፤ የያዕቆብ አምላክ ሆይ፤ ፊትህን የሚፈልግ እንዲህ ያለ ነው። ሴላ እናንተ ደጆች፤ ቀና በሉ፤ እናንተ የዘላለም በሮች፤ የክብር ንጉሥ እንዲገባ ብድግ በሉ! ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? እግዚአብሔር ነው ብርቱና ኀያል፤ እግዚአብሔር ነው በውጊያ ኀያል። እናንተ ደጆች፤ ቀና በሉ፤ እናንተ የዘላለም በሮች፤ የክብር ንጉሥ እንዲገባ ብድግ በሉ! ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እርሱ የክብር ንጉሥ ነው። ሴላ
መዝሙር 24:1-10