Psalms 104:24-30

እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች። ይህች ባሕር ሰፊና የተንጣለለች ናት፤ ታላላቅና ታናናሽ እንስሳት፣ ስፍር ቍጥር የሌላቸውም የሚርመሰመሱ ፍጥረታት በውስጧ አሉ። መርከቦች በላይዋ ይመላለሳሉ፤ አንተ የፈጠርኸውም ሌዋታን በውስጧ ይፈነጫል። ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸው ዘንድ፣ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ። በሰጠሃቸውም ጊዜ፣ አንድ ላይ ያከማቻሉ፤ እጅህንም ስትዘረጋ፣ በመልካም ነገር ይጠግባሉ። ፊትህን ስትሰውር፣ በድንጋጤ ይሞላሉ፤ እስትንፋሳቸውንም ስትወስድባቸው ይሞታሉ፤ ወደ ዐፈራቸውም ይመለሳሉ። መንፈስህን ስትልክ፣ እነርሱ ይፈጠራሉ፤ የምድርንም ገጽ ታድሳለህ።
መዝሙር 104:24-30