Proverbs 11:1-31

እግዚአብሔር የተጭበረበረ ሚዛንን ይጸየፋል፤ ትክክለኛ መለኪያ ግን ደስ ያሠኘዋል። ትዕቢት ስትመጣ ውርደትም ትከተላለች፤ በትሑት ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች። ቅኖችን ትክክለኛነታቸው ትመራቸዋለች፤ ወስላቶች ግን በገዛ አታላይነታቸው ይጠፋሉ። በቍጣ ቀን ሀብት ፋይዳ የለውም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ትታደጋለች። ለፍጹማን ሰዎች ጽድቃቸው መንገዳቸውን ታቃናላቸዋለች፤ ክፉዎች ግን በገዛ ክፋታቸው ይወድቃሉ። ቅኖችን ጽድቃቸው ትታደጋቸዋለች፤ ወስላቶች ግን በክፉ ምኞታቸው ይጠመዳሉ። ክፉ ሰው ሲሞት ተስፋው ከንቱ ትሆናለች፤ በኀይሉ የተመካበትም ሁሉ እንዳልነበረ ይሆናል። ጻድቅ ከመከራ ይድናል፤ ይልቁን መከራው በክፉው ላይ ይደርሳል። ክፉ ሰው ባልንጀራውን በአፉ ያጠፋል፤ ጻድቃን ግን በዕውቀት ያመልጣሉ። ጻድቃን ሲሳካላቸው ከተማ ደስ ይላታል፤ ክፉዎች ሲጠፉ እልልታ ይሆናል። በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፤ በክፉዎች አንደበት ግን ትጠፋለች። ልበ ቢስ ባልንጀራውን ያንኳስሳል፤ አስተዋይ ግን አንደበቱን ይገዛል። ሐሜተኛ ምስጢር አይጠብቅም፤ ታማኝ ሰው ግን ምስጢር ይጠብቃል። በአመራር ጕድለት መንግሥት ይወድቃል፤ የመካሮች ብዛት ግን ድልን ርግጠኛ ያደርጋል። ለማይታወቅ ሰው ዋስ የሚሆን መከራ ያገኘዋል፤ ዋስትና ለመስጠት እጅ የማይመታ ግን ምንም አይደርስበትም። ርኅሩኅ ሴት ክብር ታገኛለች፤ ጨካኝ ሰዎች ግን ብልጽግናን ብቻ ያገኛሉ። ደግ ሰው ራሱን ይጠቅማል፤ ጨካኝ ግን በራሱ ላይ መከራ ያመጣል። ክፉ ሰው የሚያገኘው ትርፍ መቅኖ የለውም፤ ጽድቅን የሚዘራ ግን አስተማማኝ ዋጋ ያገኛል። እውነተኛ ጻድቅ ሕይወትን ያገኛል፤ ክፋትን የሚከተል ግን ወደ ሞቱ ይጓዛል። እግዚአብሔር ልበ ጠማሞችን ይጸየፋል፤ በመንገዳቸው ነቀፋ በሌለባቸው ሰዎች ግን ደስ ይሰኛል። ክፉ ሳይቀጣ እንደማይቀር ዕወቅ፣ ጻድቃን ግን በነጻ ይሄዳሉ። በዕሪያ አፍንጫ ላይ እንደ ተሰካ የወርቅ ቀለበት፣ ማስተዋል የጐደላት ቈንጆ ሴት እንዲሁ ናት። የጻድቃን ምኞት ምን ጊዜም ፍጻሜው ያማረ ነው፤ የክፉዎች ተስፋ ግን በቍጣ ያከትማል። አንዱ በለጋስነት ይሰጣል፤ ሆኖም ይበልጥ ያገኛል፤ ሌላው ያለ መጠን ይሰስታል፤ ግን ይደኸያል። ለጋስ ይበለጽጋል፤ ሌሎችን የሚያረካም ራሱ ይረካል። በድብቅ እህል የሚያከማቸውን ሕዝብ ይረግመዋል፤ አውጥቶ የሚሸጥ ግን በረከት ይጐናጸፋል። በጎ ነገርን ተግቶ የሚሻ በጎ ነገር ይጠብቀዋል፤ ክፉ ነገር የሚፈልገውን ግን ክፉ ያገኘዋል። በሀብቱ የሚታመን ሁሉ ይወድቃል፤ ጻድቃን ግን እንደ አረንጓዴ ቅጠል ይለመልማሉ። ቤተ ሰቡን የሚያውክ ሰው ነፋስን ይወርሳል፤ ቂልም ሰው የጠቢብ ባሪያ ይሆናል። የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ናት፤ ነፍሳትን የሚማርክም ጠቢብ ነው። ጻድቅ በምድር የእጁን የሚያገኝ ከሆነ፣ ክፉውና ኀጢአተኛውማ የቱን ያህል የባሰ ያገኝ ይሆን?
ምሳሌ 11:1-31