Matthew 10:16-31

“እንግዲህ፣ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ብልኆች እንደ ርግብ የዋሃን ሁኑ። ሰዎች ይዘው ለፍርድ ወደ ሸንጎ ያቀርቧችኋል፤ በምኵራቦቻቸውም ይገርፏችኋል፤ ስለዚህ ከእነርሱ ተጠንቀቁ። በእኔ ምክንያት ወደ ገዦችና ነገሥታት ትወሰዳላችሁ፤ በእነርሱና በአሕዛብም ፊት ምስክር ትሆናላችሁ። አሳልፈው በሚሰጧችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ምን እንናገራለን፣ ምንስ እንመልሳለን ብላችሁ አትጨነቁ፤ በዚያ ጊዜ የምትናገሩት ይሰጣችኋል፤ በእናንተ የሚናገረው የሰማዩ አባታችሁ መንፈስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። “ወንድም ወንድሙን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ አባትም ልጁን፤ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያምፃሉ፤ ያስገድሏቸዋልም። ስለ ስሜ ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል፤ ነገር ግን እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል። በአንድ ስፍራ ሲያሳድዷችሁ ወደ ሌላ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁ፣ የእስራኤልን ከተሞች ሳታዳርሱ የሰው ልጅ ይመጣል። “ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፣ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም፤ ደቀ መዝሙር መምህሩን፣ ባሪያም ጌታውን ከመሰለ ይበቃዋል። ባለቤቱን ‘ብዔልዜቡል’ ካሉት፣ ቤተ ሰዎቹንማ እንዴት አብልጠው አይሏቸውም! “ስለዚህ አትፍሯቸው፤ የተሸፈነ መገለጡ፣ የተደበቀ መውጣቱ አይቀርምና። በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን አውሩት፤ በጆሯችሁ የሰማችሁትን በአደባባይ ዐውጁት፤ ሥጋን መግደል እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን ፍሩ። በአንድ ሳንቲም ከሚሸጡት ሁለት ድንቢጦች አንዲቷ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ ምድር ላይ አትወድቅም። የራስ ጠጕራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር የተቈጠረ ነው። ስለዚህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች የበለጠ ዋጋ አላችሁ።
ማቴዎስ 10:16-31