John 10:7-30

ስለዚህ ኢየሱስ ዳግም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የበጎች በር እኔ ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡት ሁሉ ሌቦችና ቀማኞች ነበሩ፤ በጎቹ ግን አልሰሟቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ሁሉ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው ሊሰርቅ፣ ሊገድልና ሊያጠፋ ብቻ ይመጣል፤ እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል፤ ተቀጣሪው እረኛ ግን በጎቹ የርሱ ስላልሆኑ፣ ተኵላ ሲመጣ ጥሏቸው ይሸሻል፤ ተኵላውም በጎቹን ይነጥቃል፤ ይበትናቸዋልም። የሚሸሸውም ተቀጣሪ ስለ ሆነና ለበጎቹ ደንታ ስለሌለው ነው። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል፤ ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው ነው። ሕይወቴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህ ጕረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት አለብኝ። እነርሱም ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። መልሼ ለማንሣት ሕይወቴን አሳልፌ ስለምሰጥ አባቴ ይወድደኛል። ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ አሳልፌ ለመስጠትም ሆነ መልሼ ለመውሰድ ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልሁትም ከአባቴ ነው።” ከዚህም ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ተፈጠረ። ብዙዎቹም፣ “ጋኔን ያደረበት እብድ ነው፤ ለምን ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎች ግን፣ “ይህ ጋኔን ያደረበት ሰው ንግግር አይደለም፤ ጋኔን የዐይነ ስውርን ዐይን መክፈት ይችላልን?” አሉ። በኢየሩሳሌምም የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ጊዜውም ክረምት ነበረ፤ ኢየሱስም በቤተ መቅደስ ግቢ፣ በሰሎሞን መመላለሻ ያልፍ ነበር፤ አይሁድም ከብበውት፣ “እስከ መቼ ልባችንን አንጠልጥለህ ታቈየናለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንህ በግልጽ ንገረን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔ ነግሬአችሁ ነበር፤ እናንተ ግን አታምኑም፤ በአባቴ ስም የማደርጋቸው ታምራትም ስለ እኔ ይናገራሉ፤ እናንተ ግን በጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም፤ በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል፤ እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም፤ ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም። እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ማንም ሊነጥቃቸው አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን።”
ዮሐንስ 10:7-30