ኢሳይያስም እንዲህ አለ፤ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፤ ስሙ! የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላኬን ትዕግሥት ትፈታተናላችሁን? ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ዐማኑኤል ትለዋለች። ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ሲችል ቅቤና ማር ይበላል። ነገር ግን ሕፃኑ ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ባድማ ይሆናል።