በሰዎች የተናቀና የተጠላ፣
የሕማም ሰውና ሥቃይ ያልተለየው ነበር።
ሰዎች ፊታቸውን እንደሚያዞሩበት ዐይነት፣
የተናቀ ነበር፤ እኛም አላከበርነውም።
በርግጥ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤
ሕመማችንንም ተሸከመ፤
እኛ ግን በእግዚአብሔር እንደ ተመታ፣
እንደ ተቀሠፈ፣ እንደ ተሠቃየም ቈጠርነው።
ነገር ግን እርሱ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤
ስለ በደላችንም ደቀቀ፤
በርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤
በርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።