Isaiah 11:1-10

ከእሴይ ግንድ ቍጥቋጥ ይወጣል፤ ከሥሮቹም አንዱ ቅርንጫፍ ፍሬ ያፈራል። የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኀይል መንፈስ፣ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስ ይለዋል። ዐይኑ እንዳየ አይፈርድም፤ ጆሮውም እንደ ሰማ አይበይንም። ነገር ግን ለድኾች በጽድቅ ይፈርዳል፤ ለምድር ምስኪኖችም ፍትሕን ይበይናል፤ በአፉ በትር ምድርን ይመታል፤ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል። ጽድቅ የወገቡ መታጠቂያ፣ ታማኝነትም የጐኑ መቀነት ይሆናል። ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋራ ይኖራል፤ ነብርም ከፍየል ግልገል ጋራ ይተኛል፤ ጥጃ፣ የአንበሳ ደቦልና የሠባ ከብት በአንድነት ይሰማራሉ፤ ትንሽ ልጅም ይመራቸዋል። ላምና ድብ በአንድነት ይሰማራሉ፤ ልጆቻቸውም ዐብረው ይተኛሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። ጡት የሚጠባ ሕፃን በአደገኛ እባብ ጕድጓድ ላይ ይጫወታል፤ ጡት የጣለም ሕፃን እጁን በእፉኝት ጕድጓድ ይከትታል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ጕዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤ ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና። በዚያም ቀን፣ የእሴይ ሥር ለሕዝቦች ምልክት ሆኖ ይቆማል፤ አሕዛብ እርሱን ይፈልጋሉ፤ ማረፊያውም የከበረ ይሆናል።
ኢሳይያስ 11:1-10