ዘፍጥረት 15:6-19

አብራም እግዚአብሔርን አመነ፤ እርሱም ጽድቅ አድርጎ ቈጠረለት። ደግሞም እግዚአብሔር፣ “ይህችን ምድር ላወርስህ፣ ከከለዳውያን ምድር፣ ከዑር ያወጣሁህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ” አለው። አብራምም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህችን ምድር እንደምወርሳት በምን ዐውቃለሁ?” አለ። እግዚአብሔርም “እያንዳንዳቸው ሦስት ዓመት የሆናቸው አንዲት ጊደር፣ አንድ ፍየልና አንድ በግ፣ በተጨማሪም አንድ ዋኖስና አንድ ርግብ ዐብረህ አቅርብልኝ” አለው። አብራምም እነዚህን ሁሉ አቀረበለት፤ ቈርጦም ሁለት ቦታ ከከፈላቸው በኋላ፣ እያንዳንዱን ክፍል በሌላው ወገን ትይዩ አስቀመጠ፤ ወፎችን ግን ለሁለት አልከፈላቸውም። አሞሮችም ሥጋውን ለመብላት ወረዱ፤ አብራም ግን አባረራቸው። ፀሓይ ልትገባ ስትል አብራም እንቅልፍ ወሰደው፤ የሚያስፈራም ድቅድቅ ጨለማ መጣበት። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ዘርህ በባዕድ አገር መጻተኛ እንደሚሆን በርግጥ ዕወቅ፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ተረግጦ ይገዛል። ነገር ግን በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እቀጣዋለሁ፤ ከዚያም ብዙ ሀብት ይዘው ይወጣሉ። አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ ዕድሜም ጠግበህ ወደ መቃብር ትወርዳለህ፤ በአራተኛውም ትውልድ ዘርህ ወደዚህ ምድር ይመለሳል፤ የአሞራውያን ኀጢአት ገና ጽዋው አልሞላምና።” ፀሓይ ገብታ ከጨለመ በኋላ የምድጃ ጢስና የሚንበለበል ፋና ታየ፤ በተከፈለውም ሥጋ መካከል ዐለፈ። በዚያ ዕለት እግዚአብሔር ለአብራም እንዲህ ሲል ኪዳን ገባለት፤ “ከግብጽ ወንዝ ጀምሮ እስከ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለውን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምሰጣቸውም የቄናውያንን፣ የቄኔዛውያንን፣ የቃድሞናውያንን፣
ዘፍጥረት 15:6-19