Exodus 14:13-22

ሙሴም ለሕዝቡ መለሰላቸው፤ “አትሸበሩ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር ዛሬ የሚያደርግላችሁን መታደግ ታያላችሁ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያንን ዳግም አታዩአቸውም። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ያለባችሁ መታገሥ ብቻ ነው።” ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለምን ትጮኹብኛላችሁ? ይልቅስ እስራኤላውያንን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ ውሃውን ለመክፈል በትርህን አንሣና እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ እስራኤላውያን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ይሻገራሉ። ተከትለዋቸው እንዲገቡም የግብጻውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ፣ በሠረገሎቹና በፈረሰኞቹ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ። በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ በከበርሁ ጊዜ፣ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” ከዚያም ከእስራኤል ሰራዊት ፊት ፊት ሆኖ ሲሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ተመለሰና ወደ ኋላቸው መጣ፤ የደመናውም ዐምድ እንዲሁ ከፊት ተነሥቶ ከኋላቸው ቆመ፤ በግብጽና በእስራኤል ሰራዊት መካከል በመሆን፣ ሌሊቱን ሙሉ ደመናው በአንድ በኩል ጨለማን ሲያመጣ፣ በሌላው በኩል ብርሃን አመጣ፤ ስለዚህ ሌሊቱን በሙሉ አንዱ ወደ ሌላው ሊጠጋ አልቻለም። ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔር ሌሊቱን በሙሉ ብርቱ የምሥራቅ ነፋስ አስነሥቶ ባሕሩን ወደ ኋላ በማሸሽ ደረቅ ምድር አደረገው፤ ውሃውም ተከፈለ። እስራኤላውያን ውሃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ በየብስ በባሕሩ ውስጥ ዐለፉ።
ዘፀአት 14:13-22