Ecclesiastes 11:1-6

እንጀራህን በውሃ ላይ ጣል፤ ከብዙ ቀን በኋላ መልሰህ ታገኘዋለህና። ሀብትህን ሰባት ቦታ፣ እንዲያውም ስምንት ቦታ ከፍለህ አስቀምጥ፤ በምድሪቱ ላይ የሚመጣውን ጥፋት አታውቅምና። ደመናት ውሃ ካዘሉ፣ በምድር ላይ ዝናብን ያዘንባሉ፤ ዛፍ ወደ ደቡብም ሆነ ወደ ሰሜን ቢወድቅ፣ በወደቀበት ቦታ በዚያ ይጋደማል። ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፤ ደመናትንም የሚያይ አያጭድም። የነፋስን መንገድ እንደማታውቅ፣ ሕይወት ወይም መንፈስ በእናት ማሕፀን ውስጥ ወደሚገኘው አካል እንዴት እንደሚገባም እንደማታውቅ ሁሉ፣ ሁሉን ሠሪ የሆነውን፣ የአምላክን ሥራ ማስተዋል አትችልም። ጧት ላይ ዘርህን ዝራ፤ ማታም ላይ እጅህ ሥራ አይፍታ፤ ይህ ወይም ያ፣ ወይም ሁለቱ መልካም ይሁኑ፣ የቱ እንደሚያፈራ አታውቅምና።
መክብብ 11:1-6