Deuteronomy 6:1-9

ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሷት ምድር እንድትጠብቁት አስተምራችሁ ዘንድ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሰጠኝ ትእዛዝ፣ ሥርዐትና ሕግ ይህ ነው፤ ይኸውም፣ የምሰጣችሁን ሥርዐቱንና ትእዛዙን ሁሉ በመጠበቅ፣ ዕድሜያችሁ እንዲረዝም፣ አንተ፣ ልጆችህና ከእነርሱ በኋላ የሚመጡት ልጆቻቸው በሕይወት ዘመናችሁ ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈሩት ዘንድ ነው። እንግዲህ እስራኤል ሆይ ስማ፤ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት፣ ማርና ወተት በምታፈስሰው ምድር መልካም እንዲሆንልህና እጅግ እንድትበዛ፣ ትእዛዙንም ትጠብቅ ዘንድ ጥንቃቄ አድርግ። እስራኤል ሆይ ስማ፤ እግዚአብሔር አምላካችን፣ እግዚአብሔር አንድ ነው። አንተም እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ። ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር። በእጅህ ላይ ምልክት አድርገህ እሰራቸው፤ በግንባርህም ላይ ይሁኑ። በቤትህ መቃኖችና በግቢህም በሮች ላይ ጻፋቸው።
ዘዳግም 6:1-9