Colossians 1:13-20

እርሱ ከጨለማ አገዛዝ ታደገን፤ ወደሚወድደው ልጁ መንግሥትም አሻገረን፤ በርሱም ቤዛነትን በደሙ አግኝተናል፤ ይህም የኀጢአት ይቅርታ ነው። እርሱ የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ ነገር በርሱ ተፈጥሯል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በርሱና ለርሱ ተፈጥሯል። እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በርሱ ነው። እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር የበላይነት ይኖረው ዘንድ እርሱ የመጀመሪያ፣ ከሙታን መካከልም በኵር ነው። እግዚአብሔርም ሙላቱ ሁሉ በርሱ ይሆን ዘንድ ወድዷልና፤ በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ ሰላምን በማድረግ፣ በምድርም ሆነ በሰማይም ያለውን ነገር ሁሉ በርሱ በኩል ከራሱ ጋራ አስታረቀ።
ቈላስይስ 1:13-20