ሶፎንያስ 3:14-20

ሶፎንያስ 3:14-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ዘምሪ፣ እስራኤል ሆይ፥ እልል በል፣ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ በፍጹም ልብሽ ሐሴት አድርጊ ደስም ይበልሽ። እግዚአብሔር ፍርድሽን አስወግዶአል፥ ጠላትሽንም ጥሎአል፣ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከልሽ አለ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አታዪም። በዚያን ቀን ለኢየሩሳሌም፦ ጽዮን ሆይ፥ አትፍሪ፥ እጆችሽም አይዛሉ። አምላክሽ እግዚአብሔር በመካከልሽ ታዳጊ ኃያል ነው፣ በደስታ በአንቺ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩም ያርፋል፥ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል ይባላል። ከጉባኤው ርቀው የሚያዝኑትን፥ ከአንቺም የሆኑትን እሰበስባለሁ፣ ስድብ እንደ ሸክም ከብዶባቸው ነበር። በዚያ ዘመን እነሆ፥ ባስጨነቁሽ ሁሉ ላይ አደርግባቸዋለሁ፣ አንካሳይቱንም አድናለሁ፥ የተጣለችውንም እሰበስባታለሁ፣ ባፈሩባትም ምድር ሁሉ ላይ ለምስጋናና ለከበረ ስም አደርጋቸዋለሁ። በዚያ ዘመን አስገባችኋለሁ፥ በዚያም ዘመን እሰበስባችኋለሁ፣ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

ሶፎንያስ 3:14-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፤ እልል በዪ፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፤ በፍጹም ልብሽ ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ። እግዚአብሔር ቅጣትሽን አስወግዶታል፤ ጠላቶችሽን ከአንቺ መልሷል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነው፤ ከእንግዲህ ወዲያ አንዳች ክፉ ነገር አትፈሪም። በዚያ ቀን ኢየሩሳሌምን እንዲህ ይሏታል፤ “ጽዮን ሆይ፤ አትፍሪ፤ እጆችሽም አይዛሉ። እግዚአብሔር አምላክሽ በመካከልሽ አለ፤ እርሱ ብርቱ ታዳጊ ነው፤ በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤ በዝማሬም በአንቺ ላይ ከብሮ ደስ ይሰኛል።” “ስለ ክብረ በዓላት መተጓጐል የተከዝሽበትን፣ የስድብሽን ሸክም፤ ከአንቺ አስወግዳለሁ። በዚያ ጊዜ፣ ያስጨነቁሽን ሁሉ እቀጣለሁ፤ ዐንካሶችን እታደጋለሁ፤ የተበተኑትንም እሰበስባለሁ፤ በተዋረዱበት ምድር ሁሉ፣ ለውዳሴና ለክብር አደርጋቸዋለሁ። በዚያ ጊዜ እሰበስባችኋለሁ፤ ያን ጊዜ ወደ አገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ ዐይናችሁ እያየ፣ ምርኳችሁን በምመልስበት ጊዜ፣ መከበርንና መወደስን፣ በምድር ሕዝብ ሁሉ መካከል እሰጣችኋለሁ”፤ ይላል እግዚአብሔር።

ሶፎንያስ 3:14-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ዘምሪ፥ እስራኤል ሆይ፥ እልል በል፥ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ በፍጹም ልብሽ ሐሴት አድርጊ ደስም ይበልሽ። እግዚአብሔር ፍርድሽን አስወግዶአል፥ ጠላትሽንም ጥሎአል፥ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከልሽ አለ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አታዪም። በዚያን ቀን ለኢየሩሳሌም፦ ጽዮን ሆይ፥ አትፍሪ፥ እጆችሽም አይዛሉ። አምላክሽ እግዚአብሔር በመካከልሽ ታዳጊ ኃያል ነው፥ በደስታ በአንቺ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩም ያርፋል፥ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል ይባላል። ከጉባኤው ርቀው የሚያዝኑትን፥ ከአንቺም የሆኑትን እሰበስባለሁ፥ ስድብ እንደ ሸክም ከብዶባቸው ነበር። በዚያ ዘመን እነሆ፥ ባስጨነቁሽ ሁሉ ላይ አደርግባቸዋለሁ፥ አንካሳይቱንም አድናለሁ፥ የተጣለችውንም እሰበስባታለሁ፥ ባፈሩባትም ምድር ሁሉ ላይ ለምስጋናና ለከበረ ስም አደርጋቸዋለሁ። በዚያ ዘመን አስገባችኋለሁ፥ በዚያም ዘመን እሰበስባችኋለሁ፥ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

ሶፎንያስ 3:14-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የጽዮን ልጅ ሆይ! ዘምሪ! የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ዘምሩ! እልልም በሉ! የኢየሩሳሌምም ሕዝብ ሆይ! በሙሉ ልባችሁ ደስ ይበላችሁ! ሐሴትም አድርጉ። እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ያስተላለፈውን የቅጣት ፍርድ አንሥቶላችኋል፤ ጠላቶቻችሁንም አስወግዶላችኋል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ነው፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጥፋት ይደርስብናል ብላችሁ አትፈሩም። በዚያን ጊዜ ስለ ኢየሩሳሌም እንደዚህ ይባልላታል፤ “የጽዮን ከተማ ሆይ! አትፍሪ! ክንዶችሽም አይዛሉ! እግዚአብሔር አምላክሽ ከአንቺ ጋር ነው፤ በኀይሉም ድልን ያጐናጽፍሻል፤ እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩም ያድስሻል፤ ሕዝቦች በበዓል ቀን በመዝሙር እንደሚያደርጉት፥ እርሱ በአንቺ ይደሰታል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በበዓል ቀን እንደሚደረገው የደስታ ስሜት እንዲሰማሽ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ምንም ኀፍረት አይደርስብሽም። የሚያስጨንቁሽን ሁሉ በዚያን ጊዜ እቀጣለሁ፤ ያነከሱትን ሁሉ አድናለሁ፤ የተገለሉትን መልሼ እሰበስባቸዋለሁ፤ ኀፍረት እንዲሰማቸው ተደርገው በነበሩበት ቦታ ሁሉ ኀፍረታቸውን ወደ ምስጋናና ክብር እለውጣለሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ጊዜ ሰብስቤ ወደ ሀገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ ንብረታችሁን ሁሉ ዐይናችሁ እያየ በምመልስላችሁ ጊዜ በምድር ሕዝቦች ሁሉ ፊት ዝነኞችና የተመሰገናችሁ ትሆናላችሁ።”

ሶፎንያስ 3:14-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፥ እልል በሉ፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ በፍጹም ልብሽ ሐሴት አድርጊ ደስም ይበልሽ። ጌታ ቅጣትሽን አስወግዷል፥ ጠላትሽንም አጥፍቷል፤ የእስራኤል ንጉሥ ጌታ በመካከልሽ አለ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አትፈሪም። በዚያን ቀን ኢየሩሳሌም እንዲህ ይባልላታል፦ “ጽዮን ሆይ፥ አትፍሪ፥ እጆችሽም አይዛሉ። ጌታ አምላክሽ በመካከልሽ ኃያል ታዳጊ ነው፤ በአንቺም በፍጹም በደስታ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩም ያርፋል፥ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል።” ከበዓሉ ርቀው የሚያዝኑትን፥ ከአንቺም የሆኑትን እሰበስባለሁ፤ ስድብ እንደ ሸክም ከብዶባቸው ነበር። እነሆ በዚያ ዘመን፥ ያስጨነቁሽን ሁሉ እቀጣለሁ፤ አንካሳይቱንም አድናለሁ፥ የተጣለችውንም እሰበስባታለሁ፤ ባፈሩባትም ምድር ሁሉ ላይ ለምስጋናና ለከበረ ስም አደርጋቸዋለሁ። በዚያ ዘመን እሰበስባችኋለሁ፥ በሰበሰብኳችሁም ጊዜ፤ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር ሕዝቦች ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል ጌታ።