ዘካርያስ 14:1-5

ዘካርያስ 14:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የእግዚአብሔር ፍርድ ቀን ደርሶአል፤ በዚያን ጊዜ ዐይናችሁ እያየ በዝባዦች ከእናንተ የወሰዱትን ይካፈሉታል። ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ እግዚአብሔር ሕዝቦችን ሰብስቦ ይመጣል፤ ከተማይቱ ትያዛለች፤ ቤቶች ይበዘበዛሉ፤ ሴቶች ይደፈራሉ፤ ከሕዝቡም እኩሌታው ተማርኮ ይሄዳል፤ የቀሩት ግን ከከተማይቱ አይወጡም። ከዚያን በኋላ እግዚአብሔር በጦርነት ጊዜ እንደሚዋጋ ሕዝቦችን ለመውጋት ይነሣል። በዚያን ቀን እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ባለው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማል፤ የደብረ ዘይት ተራራም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በሰፊ ሸለቆ በሁለት ይከፈላል፤ ስለዚህም የተራራው እኩሌታ ወደ ሰሜን እኩሌታውም ወደ ደቡብ ፈቀቅ ይላል። እናንተም ተራራውን በሁለት ከፍሎ እስከ አጻል በደረሰው በዚህ ሸለቆ ውስጥ አልፋችሁ ታመልጣላችሁ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያ ዘመን ምድር በተናወጠች ጊዜ የቀድሞ አባቶቻችሁ በሸሹት ዐይነት ትሸሻላችሁ፤ እግዚአብሔር አምላኬም ቅዱሳኑን አስከትሎ ይመጣል።

ዘካርያስ 14:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እነሆ፥ ከእናንት የተወሰድ ምርኮ በመካከላችሁ ለክፍፍል የሚበቃበት የጌታ ቀን ይመጣል። አሕዛብንም ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ እንዲነሱ እሰበስባቸዋለሁ፤ ከተማይቱም ትያዛለች፥ ቤቶችም ይበዘበዛሉ፥ ሴቶችም ይደፈራሉ፤ የከተማይቱም እኩሌታ ለምርኮ ይጋዛል፥ የቀረው ሕዝብ ግን ከከተማዋ አይፈናቃልም። ጌታም ይወጣል፥ በጦርነትም ቀን እንደሚዋጋ ከእነዚያ አሕዛቦች ጋር ይዋጋል። በዚያም ቀን የእግዚአብሔር እግሮች በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም በመካከሉ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ይሰነጠቃል፥ እጅግም ጥልቅ ሸለቆ ይሆናል፤ የተራራውም እኩሌታ ወደ ሰሜን፥ እኩሌታውም ወደ ደቡብ ይሸሻል። የተራሮችም ሸለቆ እስከ አጸል ስለሚደርስ፥ በተራሮች መካከል ባለው ሸለቆ ትሸሻላችሁ። በይሁዳም ንጉሥ በዖዝያን ዘመን በምድር መንቀጥቀጥ ምክንያት ከሆነው ሽሽት በበለጠ ትሸሻላችሁ። ከዚያም አምላኬ ጌታ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ይመጣል።