ቲቶ 1:1-9
ቲቶ 1:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእግዚአብሔር ለተመረጡት እምነት እንዲሆንላቸው በዘላለምም ሕይወት ተስፋ እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁ የተላከ፤ ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ ሰጠ። በዘመኑም ጊዜ መድኃኒታችን እግዚአብሔር እንዳዘዘ፥ ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን ገለጠ፤ በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ልጄ ለሚሆን ለቲቶ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከመድኃኒታችንም ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን። ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፥ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ፤ የማይነቀፍና የአንዲት ሚስትባል የሚሆን፥ የሚያምኑም ልጆች ያሉት፥ ስለ መዳራትም ወይም ስለ አለመታዘዝ የማይከሰስ ማንም ቢኖር፥ ሹመው። ኤጲስቆጶስ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛ ረብ የማይወድ፥ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን፤ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና።
ቲቶ 1:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የእግዚአብሔርን ምርጦች እምነትና ወደ እውነተኛ መንፈሳዊነት የሚመራውን የእውነት ዕውቀት ለማሳደግ የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነው ጳውሎስ፤ እምነቱና ዕውቀቱ የተመሠረቱትም የማይዋሸው አምላክ ከዘመናት በፊት በገባው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ላይ ነው። እርሱ በወሰነውም ጊዜ በአዳኛችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ለእኔ ዐደራ በተሰጠ ስብከት በኩል ቃሉን ይፋ አደረገ። በምንጋራው እምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነው ለቲቶ፤ ከእግዚአብሔር አብ፣ ከአዳኛችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ሰላም ይሁን። አንተን በቀርጤስ የተውሁህ ገና ያልተስተካከለውን ነገር እንድታስተካክልና ባዘዝሁህ መሠረት በየከተማው ሽማግሌዎችን እንድትሾም ነው። ሽማግሌ ነቀፋ የሌለበት፣ የአንዲት ሚስት ባል፣ ልጆቹም አማኞችና በመዳራት ወይም ባለመታዘዝ ስማቸው የማይነሣ ይሁን። ኤጲስ ቆጶስ የእግዚአብሔር ሥራ ባለዐደራ እንደ መሆኑ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባል፤ ይኸውም ትምክሕተኛ፣ ግልፍተኛ፣ ሰካራም፣ ጨቅጫቃና ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለጥቅም የሚሮጥ ሊሆን አይገባም። ከዚህ ይልቅ እንግዳ ተቀባይ፣ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድድ፣ ራሱን የሚገዛ፣ ቅን፣ ቅዱስና ጠንቃቃ ሊሆን ይገባል። ሌሎችን ትክክል በሆነው ትምህርት እንዲያበረታታና ይህንኑ ትምህርት የሚቃወሙትን ይወቅሥ ዘንድ እንደ ተማረው በታመነ ቃል የሚጸና መሆን አለበት።
ቲቶ 1:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእግዚአብሔር ለተመረጡት እምነት እንዲሆንላቸው በዘላለምም ሕይወት ተስፋ እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁ የተላከ፤ ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ ሰጠ፥ በዘመኑም ጊዜ፥ መድኃኒታችን እግዚአብሔር እንዳዘዘ፥ ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን ገለጠ፤ በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ልጄ ለሚሆን ለቲቶ፦ ከእግዚአብሔር አብ ከመድኃኒታችንም ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን። ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም፥ እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፥ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ፤ የማይነቀፍና የአንዲት ሚስትባል የሚሆን፥ የሚያምኑም ልጆች ያሉት፥ ስለ መዳራትም ወይም ስለ አለመታዘዝ የማይከሰስ ማንም ቢኖር፥ ሹመው። ኤጲስቆጶስ፥ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ፥ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛ ረብ የማይወድ፥ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን፤ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና።
ቲቶ 1:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእግዚአብሔር አገልጋይና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው፥ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች ለማጠንከርና የሃይማኖትንም እምነት ሙሉ በሙሉ እንዲያውቁ ለማድረግ ከተሾመ ከጳውሎስ የተላከ፦ ይህም እምነት በዘለዓለም ሕይወት ተስፋ ላይ የተመሠረተ ነው፤ የማይዋሸው አምላክ ይህን ሕይወት ለመስጠት ከዘመናት በፊት ቃል ገባልን። ዘመኑም በደረሰ ጊዜ በአዳኛችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ እኔ እንዳበሥር በተሰጠኝ ዐደራ አማካይነት እግዚአብሔር ቃሉን ገለጠ። የጋራችን በሆነው እምነት በእውነት ልጄ ለሆንከው ለቲቶ፥ ከእግዚአብሔር አብና ከአዳኛችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለአንተ ይሁን። አንተን በቀርጤስ የተውኩበት ምክንያት ያልተስተካከለውን እንድታስተካክልና ባዘዝኩህም መሠረት የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን በየከተማው እንድትሾም ነው። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ የማይነቀፍና የአንዲት ሚስት ባል የሆነ፥ ስድ በመሆንና ባለመታዘዝ ምክንያት የማይወቀሱ አማኞች ልጆች ያሉት ሰው መሆን ይገባዋል። ኤጲስ ቆጶስ (የቤተ ክርስቲያን መሪ) የእግዚአብሔርን ሥራ በዐደራ የተቀበለ ስለ ሆነ የማይነቀፍ መሆን አለበት፤ እንዲሁም የማይኰራ፥ በቶሎ የማይቈጣ፥ የማይሰክር፥ ጠበኛ ያልሆነ፥ ለገንዘብ የማይስገበገብ መሆን አለበት። ይልቅስ እንግዳ ተቀባይ፥ መልካም የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ራሱን የሚቈጣጠር፥ ትክክለኛ፥ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ፥ በመጠን የሚኖር ይሁን። እውነተኛውን ትምህርት በማስተማር ለመምከርና ለተቃዋሚዎችም መልስ ለመስጠት እንዲችል በተማረው መሠረት በአስተማማኝ ቃል ይጽና።
ቲቶ 1:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የእግዚአብሔር ባርያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእግዚአብሔርም የተመረጡት ያላቸውን እምነትና እግዚአብሔርን በመምሰል ላይ የተመሠረተውን የእውነት እውቀት ለማስፋፋት፥ ከቶውኑ የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ቃል በገባው የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ ያደረገ፤ ተገቢም በሆነው በራሱ ጊዜ፥ በአዳኛችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ፥ ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት አማካይነት ቃሉን ገለጠ፤ የጋራ በሆነው እምነት እውነተኛ ልጄ ለሆንከው ለቲቶ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከአዳኛችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ሰላም ይሁን። የተቀረውን ሥራ እንድታቃናና በየከተማው እኔ እንዳዘዝሁህ ሽማግሌዎችን እንድትሾም፥ አንተን በዚህ ምክንያት በቀርጤስ ተውሁህ፤ ነቀፋ የሌለበትና የአንዲት ሚስት ባል የሆነ፥ በመዳራትም ወይም ባለመታዘዝ የማይከሰሱ አማኝ ልጆች ያሉት ማንም ሰው ቢኖር፥ ሹመው። ኤጲስ ቆጶስ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ ነቀፋ የሌለበት ሊሆን ይገባዋል፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ ጠበኛ ያልሆነ፥ ለገንዘብ የማይስገበገብ፥ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚቈጣጠር ይሁን፤ እውነተኛውንም ትምህርት ለመምከርና ተቃዋሚዎቹን ለመገሠጽ እንዲችል፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና።