ማሕልየ መሓልይ 1:1-17
ማሕልየ መሓልይ 1:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር። በአፉ አሳሳም ይስመኛል፥ ጡቶችሽ ከወይን ይልቅ ያማሩ ናቸው። የሽቱሽ መዓዛ ከሽቱ ሁሉ መዓዛ ያማረ ነው፥ ስምህ እንደሚፈስስ ሽቱ ነው፤ ስለዚህ ደናግል ወደዱህ። ከወደ ኋላህም ሳቡህ፥ በሽቱህ መዓዛም እንሮጣለን፤ ንጉሡ ወደ እልፍኙ አገባኝ፤ በአንቺ ደስ ይለኛል፥ ሐሤትም እናደርጋለን፤ ከወይን ጠጅ ይልቅ ጡቶችሽን እንወዳለን፤ አንቺንም መውደድ የተገባ ነው። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እኔ ጥቁር ነኝ፤ ነገር ግን ውብ ነኝ፥ እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞንም መጋረጃዎች። ፀሓይ መልኬን አክስሎታልና ጥቁር ስለ ሆንሁ አትዩኝ፤ የእናቴ ልጆች ስለ እኔ ተጣሉ፥ የወይን ቦታዎችንም ጠባቂ አደረጉኝ፤ ነገር ግን የእኔን የወይን ቦታ አልጠበቅሁም። ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ፤ በባልንጀሮችህ መንጎች መካከል የተቅበዘበዝሁ እንዳልሆን፥ ወዴት ታሰማራለህ? በቀትርስ ጊዜ ወዴት ትመሰጋለህ? አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ያላወቅሽ እንደ ሆነ የመንጎችን ፍለጋ ተከትለሽ ውጪ፥ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞች ድንኳኖች አጠገብ አሰማሪ። ወዳጄ ሆይ፥ በፈርዖን ሰረገሎች እንዳለ ፈረሴ መሰልሁሽ። ጕንጮችሽ እንደ ዋኖስ እጅግ ያማሩ ናቸው፥ አንገትሽም በዕንቍ ድሪ ያማረ ነው። ባለ ብር ጕብጕብ የሆነ የወርቅ ጠልሰም ያድርጉልሽ። ንጉሡ በማዕድ እስከሚቀርብ ድረስ፥ የእኔ ናርዶስ መዓዛውን ሰጠ። ውዴ ለእኔ በጡቶች መካከል እንደሚያርፍ እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው። ልጅ ወንድሜ ለእኔ በዐይንጋዲ ወይን ቦታ እንዳለ እንደ አበባ ዕቅፍ ነው። ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፤ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፤ ዐይኖችሽም እንደ ርግቦች ናቸው። ልጅ ወንድሜ ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ውብ ነህ፥ መልከ መልካምም ነህ፤ አልጋችንም ለምለም ነው። የቤታችን ሰረገላ የዝግባ ዛፍ ነው፥ የጣሪያችንም ማዋቀሪያ የጥድ ዛፍ ነው።
ማሕልየ መሓልይ 1:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር። በከንፈሩ መሳም ይሳመኝ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ ደስ ያሰኛልና። የሽቱህ መዐዛ ደስ ያሰኛል፤ ስምህ እንደሚፈስስ ሽቱ ነው፤ ታዲያ ቈነጃጅት ቢወድዱህ ምን ያስደንቃል! ይዘኸኝ ሂድ፤ እንፍጠን! ንጉሡ ወደ ዕልፍኞቹ አምጥቶኛል። በአንተ ደስ ይለናል፤ ሐሤትም እናደርጋለን፤ ከወይን ጠጅ ይልቅ ፍቅርህን እንወድሳለን። አንተን እንደዚህ ማፍቀራቸው ትክክል ነው። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፤ እኔ ጥቍር ነኝ፤ ይሁን እንጂ ውብ ነኝ፤ ጥቍረቴ እንደ ቄዳር ድንኳኖች፣ እንደ ሰሎሞን ቤተ መንግሥት መጋረጃዎችም ነው። ጥቍር ስለ ሆንሁ ትኵር ብላችሁ አትዩኝ፤ መልኬን ያጠቈረው ፀሓይ ነውና፤ የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ተቈጡኝ፤ የወይን ተክል ቦታዎችም ጠባቂ አደረጉኝ፤ የራሴን የወይን ተክል ቦታ ተውሁት። ውዴ ሆይ፤ መንጋህን የት እንደምታሰማራ፣ በቀትርም የት እንደምትመስጋቸው እባክህ ንገረኝ፤ በወዳጆችህ መንጎች ኋላ፣ ፊቷን ሸፍና እንደምትቅበዘበዝ ሴት ለምን ልሁን? አንቺ ከሴቶች ሁሉ ይበልጥ የተዋብሽ ሆይ፤ የማታውቂ ከሆነ፣ የበጎቹን ዱካ ተከተዪ፤ የፍየል ግልገሎችሽንም፣ በእረኞቹ ድንኳን አጠገብ አሰማሪ። ውዴ ሆይ፤ የፈርዖንን ሠረገሎች ከሚስቡ ፈረሶች መካከል፣ በአንዲቱ ባዝራ መሰልሁሽ። ጕንጮችሽ በጕትቻ፣ ዐንገትሽም በዕንቍ ሐብል አጊጠዋል። እኛም ባለብር ፈርጥ፣ የወርቅ ጕትቻ እናሠራልሻለን። ንጉሡ ማእዱ ላይ ሳለ፣ የእኔ ናርዶስ መዐዛውን ናኘው። ውዴ ለእኔ በጡቶቼ መካከል እንዳረፈ፣ በመቋጠሪያ እንዳለ ከርቤ ነው። ውዴ ለእኔ ከዓይንጋዲ የወይን ተክል ቦታ እንደ መጣ የሄና አበባ ዕቅፍ ነው። ውዴ ሆይ፤ እንዴት ውብ ነሽ! እንዴትስ ያለሽ ቈንጆ ነሽ! ዐይኖችሽም እንደ ርግብ ዐይኖች ናቸው። አንተ ውዴ ሆይ፤ እንዴት ውብ ነህ! እንዴትስ ታምራለህ! ዐልጋችንም እንደ ለምለም ሣር ነው። የቤታችን ተሸካሚዎች ዝግባዎች፣ የጣራችን ማዋቀሪያዎችም ጥዶች ናቸው።
ማሕልየ መሓልይ 1:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር። በአፉ መሳም ይሳመኝ፥ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና። ዘይትህ መልካም መዓዛ አለው፥ ስምህ እንደሚፈስስ ዘይት ነው፥ ስለዚህ ደናግል ወደዱህ። ሳበኝ፥ ከአንተም በኋላ እንሮጣለን፥ ንጉሥ ወደ ቤቱ አገባኝ፥ በአንተ ደስ ይለናል፥ ሐሤትም እናደርጋለን፥ ከወይን ጠጅ ይልቅ ፍቅርህን እናስባለን፥ በቅንነት ይወድዱሃል። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እኔ ጥቁር ነኝ፥ ነገር ግን ውብ ነኝ፥ እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞንም መጋረጃዎች። ፀሐይ መልኬን አክስሎታልና ጥቁር ስለ ሆንሁ አትዩኝ፥ የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ፥ የወይን ቦታዎችንም ጠባቂ አደረጉኝ፥ ነገር ግን የእኔን ወይን ቦታ አልጠበቅሁም። ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ፥ ወዴት ታሰማራለህ? በቀትርስ ጊዜ ወዴት ትመስጋለህ? ስለ ምንስ ከባልንጀሮችህ መንጎች በኋላ እቅበዘበዛለሁ? አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ያላወቅሽ እንደ ሆነ የመንጎችን ፍለጋ ተከትለሽ ውጪ፥ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞች ድንኳኖች አጠገብ አሰማሪ። ወዳጄ ሆይ፥ በፈርዖን ሰረገሎች እንዳለ ፈረስ መሰልሁሽ። የጕንጭሽ ውበት በከበረ ሉል፥ አንገትሽም በዕንቍ ድሪ ያማረ ነው። ባለ ብር ጕብጕብ የሆነ የወርቅ ጠልሰም እናደርግልሻለን። ንጉሡ በማዕዱ ሳለ፥ የእኔ ናርዶስ መዓዛውን ሰጠ። ውዴ ለእኔ በጡቶቼ መካከል እንደሚያርፍ እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው። ውዴ ለእኔ በዓይንጋዲ ወይን ቦታ እንዳለ እንደ አበባ እቅፍ ነው። ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፥ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፥ ዓይኖችሽም እንደ ርግቦች ናቸው። ውዴ ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ውብ ነህ፥ መልከ መልካምም ነህ፥ አልጋችንም ለምለም ነው። የቤታችን ሰረገላ የዝግባ ዛፍ ነው፥ የጣሪያችንም ማዋቀሪያ የጥድ ዛፍ ነው።
ማሕልየ መሓልይ 1:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከሰሎሞን መዝሙሮች መካከል በጣም ውብ የሆነው መዝሙር። ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ ጣዕም ያለው ስለ ሆነ፥ ከንፈሮችህ ይሳሙኝ። የምትቀባው ሽቱ መልካም መዓዛ አለው፤ ስምህን መጥራት ሽቱን እንደ መርጨት ነው፤ ቈነጃጅትም የሚያፈቅሩህ ስለዚህ ነው። እጄን ይዘህ ሳበኝ፤ አብረን እንሩጥ። ንጉሡ ወደ እልፍኙ አስገባኝ፤ በዚያም አብረን ደስ ይለናል፤ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ ያስደስታል፤ ስለዚህ ቈነጃጅት ሁሉ እጅግ ያፈቅሩሃል። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ! ስሙኝ፤ እኔ ጥቊር ነኝ፤ ይሁን እንጂ ውብ ነኝ፤ የመልኬ ጥቊረት እንደ ቄዳር ድንኳን ነው፤ ውበቴ ግን እንደ ሰሎሞን ቤተ መንግሥት መጋረጃዎች ነው። መልኬን ያጠቈረው የፀሐይ ቃጠሎ ነው፤ ስለዚህ ጥቊር በመሆኔ አትናቁኝ፤ የእናቴ ልጆች የሆኑ ወንድሞቼ ስለ ተጣሉኝ የወይን ተክል ጠባቂ አደረጉኝ፤ ስለዚህ የግሌ የወይን ተክል ለመጠበቅ ጊዜ አልነበረኝም። ውዴ ሆይ! እስቲ ንገረኝ፤ የበጎችህን መንጋ የምታሰማራው የት ነው? በቀትርስ ጊዜ ዕረፍት ያገኙ ዘንድ እንዲመሰጉ የምታደርገው የት ነው? አንተን በመፈለግ የጓደኞችህን መንጋ በመከተል ፊትዋን እንደ ሸፈነች ሴት የምቅበዘበዘው ለምንድን ነው? አንቺ ከሴቶች ሁሉ ያማርሽ ውብ ሆይ! ቦታውን የማታውቂው ከሆነ የበጎቹን ዱካ ተከትለሽ ሂጂ፤ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞቹ ድንኳኖች አጠገብ አሰማሪ። ውዴ ሆይ! የፈርዖንን ሠረገሎች በሚስቡ ፈረሶች መካከል ያለችውን ውብ ባዝራ ትመስያለሽ፤ የጉንጮችሽ ውበት እንደ ከበረ ሉል ነው፤ አንገትሽም በዕንቊ ጌጥ የተዋበ ነው። እኛ ግን የብር ፈርጥ ያለው የወርቅ ጌጥ እናሠራልሻለን። ንጉሡ በድንክ አልጋው ላይ ዐረፍ ብሎ ሳለ የሽቶዬ መዓዛ ቤቱን ሁሉ ሞላው። ውዴ በጡቶቼ መካከል እንደሚያርፍ፥ መዓዛው እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው። ውዴ፥ ዔንገዲ ተብሎ በሚጠራው የወይን ተክል ቦታ እንደ በቀለ የበረሓ አበባ ነው። ፍቅሬ ሆይ! እንዴት የተዋብሽ ነሽ! እንዴትስ ያማርሽ ነሽ! ዐይኖችሽ እንደ ርግብ ውብ ናቸው። ውዴ ሆይ! አንተም እኮ ውብ ነህ፤ እጅግም ደስ ታሰኛለህ፤ አልጋችንም እንደ ለምለም ሣር ደስ የሚያሰኝ ነው። የቤታችን ምሰሶ የሊባኖስ ዛፍ ነው፤ ጣራውም በጥድ እንጨት የተዋቀረ ነው።
ማሕልየ መሓልይ 1:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር። በአፉ መሳም ይሳመኝ፥ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና። ዘይትህ መልካም መዓዛ አለው፥ ስምህ እንደሚፈስስ ዘይት ነው፥ ስለዚህ ደናግል ወደዱህ። ሳበኝ፥ ከአንተም በኋላ እንሮጣለን፥ ንጉሥ ወደ ቤቱ አገባኝ፥ በአንተ ደስ ይለናል፥ ሐሤትም እናደርጋለን፥ ከወይን ጠጅ ይልቅ ፍቅርህን እናስባለን፥ በቅንነት ይወድዱሃል። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እኔ ጥቁር ነኝ፥ ውብም ነኝ፥ እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞንም መጋረጃዎች። ፀሐይ መልኬን አክስሎታልና ጥቁር ስለ ሆንኩ አትዩኝ፥ የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ፥ የወይን ቦታዎችንም ጠባቂ አደረጉኝ፥ ነገር ግን የእኔን ወይን ቦታ አልጠበቅሁም። ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ፥ ወዴት ታሰማራለህ? በቀትርስ ጊዜ ወዴት ትመስጋለህ? ስለ ምንስ ከባልንጀሮችህ መንጎች በኋላ እቅበዘበዛለሁ? አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ያላወቅሽ እንደሆነ የመንጎችን ፍለጋ ተከትለሽ ውጪ፥ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞች ድንኳኖች አጠገብ አሰማሪ። ወዳጄ ሆይ፥ በፈርዖን ሰረገሎች እንዳለ ፈረስ መሰልሁሽ። የጉንጭሽ ውበት በከበረ ሉል፥ አንገትሽም በዕንቁ ድሪ ያማረ ነው። ባለ ብር ጉብጉብ የሆነ የወርቅ ጠልሰም እናደርግልሻለን። ንጉሡ በማዕዱ ሳለ፥ የእኔ ናርዶስ መዓዛውን ሰጠ። ውዴ ለእኔ በጡቶቼ መካከል እንደሚያርፍ እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው። ውዴ ለእኔ በዓይንጋዲ ወይን ቦታ እንዳለ እንደ አበባ እቅፍ ነው። ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፥ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፥ ዐይኖችሽም እርግቦች ናቸው። ውዴ ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ውብ ነህ፥ መልከ መልካምም ነህ፥ አልጋችንም ለምለም ነው። የቤታችን ሠረገላ የዝግባ ዛፍ ነው፥ የጣሪያችንም ማዋቀሪያ የጥድ ዛፍ ነው።