ሩት 2:1-6
ሩት 2:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለኑኃሚንም ባል የሚዛመደው ከአቤሜሌክ ወገን የሆነ ኃያል ሰው ስሙ ቦዔዝ የተባለ ሰው ነበረ። ሞዓባዊቱም ሩት ኑኃሚንን፦ በፊቱ ሞገስ የማገኘውን ተከትዬ እህል እንድቃርም ወደ እርሻ ልሂድ አለቻት። እርስዋም፦ ልጄ ሆይ፥ ሂጂ አለቻት። ሄደችም፥ ከአጫጆችም በኋላ በእርሻ ውስጥ ቃረመች፣ እንደ አጋጣሚውም የአቤሜሌክ ወገን ወደ ነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደረሰች። እነሆም፥ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፥ አጫጆችንም፦ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን አላቸው። እነርሱም፦ እግዚአብሔር ይባርክህ ብለው መለሱለት። ቦዔዝም በአጫጆች ላይ አዛዥ የነበረውን ሎሌውን፦ ይህች ቆንጆ የማን ናት? አለው። የአጫጆቹም አዛዥ፦ ይህችማ ከሞዓብ ምድር ከኑኃሚን ጋር የመጣች ሞዓባዊቱ ቆንጆ ናት፣
ሩት 2:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኑኃሚን፣ ከአሊሜሌክ ጐሣ የሆነ ቦዔዝ የሚባል ባለጠጋ የባል ዘመድ ነበራት። ሞዓባዊቷ ሩትም ኑኃሚንን፣ “በፊቱ ሞገስ አግኝቼ ቃርሚያ የሚያስቃርመኝ ሰው ባገኝ እስኪ ወደ እህል አዝመራው ልሂድ” አለቻት። ኑኃሚንም፣ “ልጄ ሆይ፤ ይሁን ሂጂ” አለቻት። ስለዚህ እርሷም ወጣች፤ ከዐጫጆች ኋላ ኋላ እየተከታተለችም ከአዝመራው ቦታ ትቃርም ጀመር፤ እንዳጋጣሚ ትቃርምበት የነበረው አዝመራ ከአሊሜሌክ ጐሣ የሆነው የቦዔዝ ነበር። በዚሁ ጊዜ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፤ ዐጫጆቹንም፣ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ይሁን!” ብሎ ሰላምታ ሰጣቸው። እነርሱም፣ “እግዚአብሔር ይባርክህ!” ብለው መለሱለት። ከዚያም ቦዔዝ የዐጫጆቹን አለቃ፣ “ይህች ወጣት ሴት የማን ናት?” ሲል ጠየቀው። የዐጫጆቹም አለቃ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከኑኃሚን ጋራ ከሞዓብ ምድር ተመልሳ የመጣች ሞዓባዊት ናት።
ሩት 2:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለኑኃሚንም ባል የሚዘመደው ከአቤሜሌክ ወገን የሆነ ኃያል ሰው ስሙ ቦዔዝ የተባለ ሰው ነበረ። ሞዓባዊቱም ሩት ኑኃሚንን “በፊቱ ሞገስ የማገኘውን ተከትዬ እህል እንድቃርም ወደ እርሻ ልሂድ፤” አለቻት። እርስዋም “ልጄ ሆይ! ሂጂ፤” አለቻት። ሄደችም፤ ከአጫጆችም በኋላ በእርሻ ውስጥ ቃረመች፤ እንደ አጋጣሚውም የአቤሜሌክ ወገን ወደ ነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደረሰች። እነሆም፥ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፤ አጫጆችንም “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤” አላቸው። እነርሱም “እግዚአብሔር ይባርክህ፤” ብለው መለሱለት። ቦዔዝም በአጫጆች ላይ አዛዥ የነበረውን ሎሌውን “ይህች ወጣት ሴት የማን ናት?” አለው። የአጫጆቹም አዛዥ “ይህችማ ከሞዓብ ምድር ከኑኃሚን ጋር የመጣች ሞዓባዊቱ ቆንጆ ናት፤
ሩት 2:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ለናዖሚም ሀብታምና ታዋቂ የሆነ ቦዔዝ የሚባል የባልዋ የአቤሜሌክ የቅርብ ዘመድ ነበራት፤ አንድ ቀን ሞአባዊትዋ ሩት ናዖሚን “በፊቱ ሞገስ ወደማገኝበት ሰው እርሻ ሄጄ ቃርሚያ ልቃርም” አለቻት። ናዖሚም “ልጄ ሆይ! ሂጂ!” አለቻት። ሩትም ወደ እርሻዎች ሄደች፤ ከአጫጆች ኋላ እየተከተለችም ከእጃቸው የወዳደቀውን ዛላ ትቃርም ጀመር፤ እንደ አጋጣሚ የምትቃርምበት ቦታ የአቤሜሌክ ዘመድ የሆነው የቦዔዝ እርሻ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቦዔዝ ራሱ ከቤተልሔም ተነሥቶ ወደ እርሻው መጣ፤ አጫጆቹንም “እንደምን ዋላችሁ! እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን!” አላቸው። እነርሱም “እግዚአብሔር አንተንም ይባርክህ!” አሉት። ከዚህ በኋላ ቦዔዝ የአጫጆቹ ኀላፊ የሆነውን ሰው “ያቺ ወጣት ሴት ማን ናት?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እርስዋ ናዖሚን ተከትላ ከሞአብ አገር የመጣች ሞአባዊት ናት፤
ሩት 2:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ለናዖሚም በባልዋ የሚዛመዳት ሰው ከኤሊሜሌክ ወገን የሆነ ስሙ ቦዔዝ የተባለ ኃያል ሰው ነበረ። ሞአባዊቱም ሩት ናዖሚንን፦ “በፊቱ ሞገስ ወደማገኝበት ሰው ተከትዬ እህል ለመቃረም ወደ እርሻ ልሂድ” አለቻት። እርሷም፦ “ልጄ ሆይ፥ ሂጂ” አለቻት። ስለዚህም ሄደች፥ ከአጫጆችም በኋላ በእርሻ ውስጥ ቃረመች፥ እንደ አጋጣሚም የኤሊሜሌክ ወገን ወደነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደረሰች። ከጥቂት ጊዜ በኋላም፥ ቦዔዝ ከቤተልሔም መጣ፥ አጫጆችንም፦ “ጌታ ከእናንተ ጋር ይሁን” አላቸው። እነርሱም፦ “ጌታ ይባርክህ” ብለው መለሱለት። ቦዔዝም በአጫጆች ላይ አዛዥ የነበረውን አገልጋዩን፦ “ይህች ብላቴና የማን ናት?” አለው። የአጫጆቹም አዛዥ፦ “ይህችማ ከሞዓብ ምድር ከናዖሚን ጋር የመጣች ሞዓባዊቱ ብላቴና ናት፥” ብሎ መለሰ።