ሮሜ 8:1-8 - Compare All Versions

ሮሜ 8:1-8 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))

እን​ግ​ዲህ በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ላሉት በመ​ን​ፈስ እንጂ በሥጋ ለማ​ይ​መ​ላ​ለሱ ፍርድ የለ​ባ​ቸ​ውም። በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ የተ​ሰ​ጠን ሕይ​ወት የሚ​ገ​ኝ​በት የመ​ን​ፈስ ሕግ እርሱ ከኀ​ጢ​አ​ትና ከሞት ሕግ ነጻ አው​ጥ​ቶ​ና​ልና። ስለ ሥጋ ደካ​ማ​ነት የኦ​ሪት ሕግ ከሞት ማዳን በተ​ሳ​ነው ጊዜ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በኀ​ጢ​ኣ​ተና ሥጋ ምሳሌ ልጁን ላከ፤ ያች​ንም ኀጢ​አት በሥ​ጋው ቀጣት። እናን ያጸ​ድ​ቀን ዘንድ፥ የኦ​ሪ​ት​ንም ሕግ ሠርቶ እንደ ፈጸመ ሰው ያደ​ር​ገን ዘንድ፤ ይህም በመ​ን​ፈ​ሳዊ ሕግ ጸን​ተው ለሚ​ኖሩ ነው እንጂ በሥጋ ሕግ ለሚ​ሠሩ አይ​ደ​ለም። እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚ​ኖሩ የሥ​ጋን ነገር ያስ​ባ​ሉና፤ እንደ መን​ፈስ ፈቃድ የሚ​ኖሩ ግን የመ​ን​ፈ​ስን ነገር ያስ​ባሉ። የሥጋ ዐሳብ ሞትን ያመ​ጣ​ብ​ናል፤ የመ​ን​ፈስ ዐሳብ ግን ሰላ​ም​ንና ሕይ​ወ​ትን ይሰ​ጠ​ናል። የሥጋ ዐሳብ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጠላቱ ነውና፤ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሕግ ስለ​ማ​ይ​ገዛ፥ መፈ​ጸም አይ​ቻ​ለ​ውም። ለሥ​ጋዊ ፈቃ​ዳ​ቸው የሚ​ሠሩ ሁሉ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ደስ ማሰ​ኘት አይ​ች​ሉም።

ሮሜ 8:1-8 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም፤ ምክንያቱም የሕይወት መንፈስ ሕግ በክርስቶስ ኢየሱስ ከኀጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቷችኋል። ሕግ ከሥጋ ባሕርይ የተነሣ ደክሞ ሊፈጽም ያልቻለውን፣ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኀጢአተኛ ሰው አምሳል፣ የኀጢአት መሥዋዕት እንዲሆን በመላክ ፈጸመው፤ በዚህም ኀጢአትን በሥጋ ኰነነ፤ ይኸውም በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ በምንመላለስ በእኛ፣ ሕጉ የሚጠይቀው ጽድቅ ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም ነው። እንደ ሥጋ የሚኖሩ ሐሳባቸውን በሥጋ ፍላጎት ላይ ያሳርፋሉ፤ እንደ መንፈስ የሚኖሩ ግን ሐሳባቸውን በመንፈስ ፍላጎት ላይ ያደርጋሉ። የሥጋን ነገር ማሰብ ሞት ነው፤ የመንፈስን ነገር ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ለኀጢአት የተገዛ አእምሮ ከእግዚአብሔር ጋራ ጠበኛ ነው፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛም፤ መገዛትም አይችልም። በሥጋ የሚመሩትም እግዚአብሔርን ማስደሰት አይችሉም።

ያጋሩ
ሮሜ 8 NASV

ሮሜ 8:1-8 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። ከሥጋ የተነሣ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በባንመላለስ በእኛ የሕግ ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ ኃጢአትን በሥጋ ኵኦነነ። እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም።

ሮሜ 8:1-8 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚኖሩ አሁን ኲነኔ የለባቸውም። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘውን ሕይወት የሚሰጥ የመንፈስ ቅዱስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቶኛል። ከሰው ባሕርይ ደካማነት የተነሣ ሕግ ሊያደርገው ያልቻለውን እግዚአብሔር አድርጎታል፤ የገዛ ልጁንም በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌነት በኃጢአት ምክንያት ልኮ በሥጋው ኃጢአትን በፍርድ አስወገደ። ይህንንም ያደረገው በሥጋ ፈቃድ ሳይሆን በመንፈስ ፈቃድ በምንመላለስ በእኛ ትክክለኛው የሕግ ትእዛዝ እንዲፈጸም ነው። በሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ ሥጋዊ ነገርን፥ በመንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን መንፈሳዊ ነገርን ያስባሉ። ሥጋዊ ነገርን ማሰብ ሞትን ያመጣል፤ መንፈሳዊ ነገርን ማሰብ ግን ሕይወትንና ሰላምን ይሰጣል። ሥጋዊ ነገርን የሚያስብ ሰው ለእግዚአብሔር ሕግ ስለማይታዘዝና መታዘዝም ስለማይችል የእግዚአብሔር ጠላት ነው። ለሥጋዊ ነገር የሚገዙ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይችሉም።

ሮሜ 8:1-8 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))

ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም። በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ አውጥቶኛልና። ሕግ ከሥጋ ድካም የተነሣ ማድረግ ያልቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌና ስለ ኃጢአት ልኮ ኃጢአትን በሥጋ ኰነነ፤ እንደ ሥጋ ሳይሆን እንደ መንፈስ በምንመላለስ በእኛ፥ ሕጉ የሚጠይቀው ጽድቅ እንዲፈጸም ነው። እንደ ሥጋ የሚኖሩ አእምሮአቸው የሥጋን ነገር እንዲያስብ ያደርጋሉና፥ እንደ መንፈስ የሚኖሩ ግን አእምሮአቸው የመንፈስን ነገር እንዲያስብ ያደርጋሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ የእግዚአብሔር ጠላት መሆን ነው፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም አይችልም፥ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይችሉም።