ሮሜ 5:2-5 - Compare All Versions
ሮሜ 5:2-5 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
በእርሱም አማካኝነት ወደቆምንበት ወደ ጸጋው በእምነት ተመራን፤ በእግዚአብሔርም ክብር ተስፋ እንመካለን። የምንመካ በእርስዋ ብቻ አይደለም፤ በመከራችን ደግሞ እንመካለን እንጂ፤ መከራ በእና ላይ ትዕግሥትን እንደሚያመጣ እናውቃለንና። ትዕግሥትም መከራ ነው፤ በመከራም ተስፋ ይገናል። ተስፋም አያሳፍርም፤ በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን መልቶአልና።
ሮሜ 5:2-5 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
በርሱም በኩል አሁን ወደ ቆምንበት ጸጋ በእምነት መግባት ችለናል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር ተስፋ በማድረግ ሐሤት እናደርጋለን። በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤ ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም፤ እግዚአብሔር በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅሩን በልባችን አፍስሷልና።
ሮሜ 5:2-5 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
በእርሱም ደግሞ ወደ ቆምንበት ወደዚህ ጸጋ በእምነት መግባትን አግኝተናል፤ በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ እንመካለን። ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፥ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፥ በመከራችን ደግሞ እንመካለን፤ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም።
ሮሜ 5:2-5 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ወደዚህ አሁን በእምነት ጸንተን ወደምንገኝበት ጸጋ የገባነው በእርሱ ስለ ሆነ በተስፋ የእግዚአብሔር ክብር ተካፋዮች በመሆናችን እንመካለን። በዚህ ብቻ ሳይሆን መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝልን ስለምናውቅ በመከራችንም እንመካለን። ከትዕግሥትም በፈተና መጽናት፥ ከመጽናትም ተስፋ ይገኛል። በተሰጠን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ሞላ ተስፋው አያሳፍርም።
ሮሜ 5:2-5 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
በእርሱም በኩል ወደ ቆምንበት ወደዚህ ጸጋ በእምነት መግባት ችለናል፤ በእግዚአብሔርም ክብር በተስፋ እንመካለን። በዚህ ብቻ ሳይሆን፥ መከራ ጽናትን እንደሚያስገኝ ስለምናውቅ በመከራም ጭምር እንመካለን፤ ጽናትም የተፈተነ ባሕርይን ያስገኝልናል፥ የተፈተነ ባሕርይም ተስፋን፤ ተስፋም ቅር አያሰኘንም፤ ምክንያቱም በተሰጠን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ነው።