ሮሜ 5:15-17
ሮሜ 5:15-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋው በበደላችን መጠን የሆነብን አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎች ከሞቱ፥ እንግዲህ በእግዚአብሔር ጸጋ፥ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት በሰጠን ሀብቱ ሕይወት በብዙዎች ላይ እንዴት እጅግ ይበዛ ይሆን? የእግዚአብሔር ጸጋው በአንዱ ሰው ኀጢአት መጠን የሆነብን አይደለም፤ የኀጢአት ፍርድ ከአንድ ሰው ወጥታ ሁሉ ከተቀጣባት፥ ጸጋው ከበደላችን እንደ ምን ያነጻን ይሆን? የዘለዓለምንስ ሕይወት እንዴት ይሰጠን ይሆን? የአንዱ ሰው ኀጢአት ሞትን ካነገሠችው በአንድ ሰው በደልም ሞት ከገዛን፥ የአንዱ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ የጸጋው ብዛትና የጽድቁ ስጦታ እንዴት እጅግ ያጸድቀን ይሆን? የዘለዓለም ሕይወትንስ እንዴት ያበዛልን ይሆን?
ሮሜ 5:15-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው መተላለፍ ብዙዎቹ ከሞቱ፣ የእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው፣ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የመጣው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት አብልጦ ይትረፈረፍ! ደግሞም የእግዚአብሔር ስጦታ እንደ አንዱ ሰው የኀጢአት ውጤት አይደለም፤ ምክንያቱም ፍርዱ የአንድን ሰው ኀጢአት ተከትሎ ኵነኔን አመጣ፤ ስጦታው ግን አያሌ መተላለፍን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ። በአንድ ሰው መተላለፍ ምክንያት ሞት በዚህ ሰው በኩል የነገሠ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅ ስጦታ የተቀበሉት፣ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንዴት አብልጠው በሕይወት አይነግሡ!
ሮሜ 5:15-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ። አንድ ሰውም ኃጢአትን በማድረጉ እንደ ሆነው መጠን እንደዚያው ስጦታው አይደለም፤ ፍርድ ከአንድ ሰው ለኵነኔ መጥቶአልና፥ ስጦታው ግን በብዙ በደል ለማጽደቅ መጣ። በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ።
ሮሜ 5:15-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ነገር ግን የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታው እንደ ሰው ኃጢአት አይደለም፤ በአንድ ሰው ኃጢአት ምክንያት ብዙዎች እንደ ሞቱ እንዲሁም በእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት የተገኘው የጸጋ ስጦታ ለብዙዎች ተትረፍርፎ ተሰጥቶአል። እንዲሁም የእግዚአብሔር ነጻ ስጦታው ያመጣው ጸጋ ውጤት የአንድ ሰው ኃጢአት እንዳመጣው ውጤት አይደለም። በአንድ ሰው ኃጢአት ምክንያት የተሰጠው ፍርድ ቅጣትን አመጣ፤ በብዙ ኃጢአት ምክንያት የተሰጠው ነጻ ስጦታ ጽድቅን አመጣ። በአንድ ሰው ኃጢአት ምክንያት ሞት በሰው ሁሉ ላይ ሥልጣን ካገኘ የእግዚአብሔርን የተትረፈረፈ ጸጋና ነጻ ስጦታ ተቀብለው የጸደቁ ሁሉ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በድል አድራጊነት በሕይወት ይኖራሉ።
ሮሜ 5:15-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ከሞቱ፥ ይልቁንም የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ያለው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት ይበዛ። ስጦታውም አንድ ሰው ኃጢአትን በማድረጉ እንዳመጣው ውጤት አይደለም፤ በአንድ በኩል፥ ፍርዱ የአንድን ሰው በደል ተከትሎ ኩነኔን አመጣ፤ በሌላ በኩል ግን ስጦታው ብዙ በደልን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ። በአንድ ሰው በደል ምክንያት በዚህ ሰው በኩል ሞት ከነገሠ፥ ይልቁን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅን ስጦታ የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ።