ሮሜ 4:1-12,16

ሮሜ 4:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እን​ግ​ዲህ በሥጋ የቀ​ድሞ አባ​ታ​ችን የሆ​ነው አብ​ር​ሃም ምን አገኘ እን​ላ​ለን? ይህን በሥ​ራው አግ​ኝ​ቶ​አ​ልን? አብ​ር​ሃም በሥ​ራው ጸድ​ቆስ ቢሆን ትም​ክ​ሕት በሆ​ነው ነበር፤ ነገር ግን በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ አይ​ደ​ለም። መጽ​ሐ​ፍስ ምን ይላል? አብ​ር​ሃም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አመነ፤ ጽድ​ቅም ሆኖ ተቈ​ጠ​ረ​ለት። ለሚ​ሠራ ዋጋው እን​ደ​ሚ​ገ​ባው እንጂ በለ​ጋ​ስ​ነት እንደ ሰጡት ሆኖ አይ​ቈ​ጠ​ር​በ​ትም። ለማ​ይ​ሠራ ግን ኀጢ​አ​ተ​ና​ውን በሚ​ያ​ጸ​ድ​ቀው ካመነ እም​ነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቈ​ጠ​ር​ለ​ታል። የኦ​ሪ​ትን ሥራ ሳይ​ፈ​ጽም ማመኑ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ጽድቅ ሆኖ የሚ​ቈ​ጠ​ር​ለ​ትን ሰው ዳዊት “ብፁዕ” በሚ​ል​በት አን​ቀጽ እን​ዲህ ይላል፦ “መተ​ላ​ለ​ፋ​ቸው የቀ​ረ​ላ​ቸው፥ ኀጢ​አ​ታ​ቸ​ውም የተ​ሰ​ረ​የ​ላ​ቸው ብፁ​ዓን ናቸው። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በደ​ሉን የማ​ይ​ቈ​ጥ​ር​በት ሰው ብፁዕ ነው።” እን​ግ​ዲህ ይህ ብፅ​ዕና ስለ መገ​ዘር ተነ​ገ​ረን? ወይስ ስለ አለ​መ​ገ​ዘር? እም​ነቱ ለአ​ብ​ር​ሃም ጽድቅ ሆኖ ተቈ​ጠ​ረ​ለት እን​ላ​ለ​ንና። ለአ​ብ​ር​ሃም ጽድቅ ሆኖ የተ​ቈ​ጠ​ረ​ለት መቼ ነው? ተገ​ዝሮ ሳለ ነውን? ወይስ ሳይ​ገ​ዘር? ሳይ​ገ​ዘር ነው እንጂ ተገ​ዝሮ ሳለ አይ​ደ​ለም። ሳይ​ገ​ዘር እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አብ​ር​ሃ​ምን በእ​ም​ነት እንደ አጸ​ደ​ቀው በእ​ርሱ ላይ ይታ​ወቅ ዘንድ ግዝ​ረ​ትን የጽ​ድቅ ማኅ​ተም ትሆ​ነው ዘንድ ምል​ክት አድ​ርጎ ሰጠው። ሳይ​ገ​ዘሩ ለሚ​ያ​ምኑ ሁሉ አባት ሊሆን፥ አብ​ር​ሃም በእ​ም​ነት እንደ ከበረ እነ​ር​ሱም በእ​ም​ነት እን​ደ​ሚ​ከ​ብሩ ያውቁ ዘንድ ሰጠው። ለተ​ገ​ዘ​ሩ​ትም አባት ይሆን ዘንድ ነው፤ ነገር ግን ለተ​ገ​ዘ​ሩት ብቻ አይ​ደ​ለም፤ እርሱ አባ​ታ​ችን አብ​ር​ሃም ሳይ​ገ​ዘር እንደ አመነ ሳይ​ገ​ዘሩ የአ​ባ​ታ​ችን የአ​ብ​ር​ሃ​ምን የሃ​ይ​ማ​ኖ​ቱን ፍለጋ ለሚ​ከ​ተሉ ደግሞ ነው እንጂ።

ሮሜ 4:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እንግዲህ በሥጋ የቀድሞ አባታችን የሆነ አብርሃም በዚህ ረገድ ምን አገኘ እንላለን? አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢሆን ኖሮ፣ የሚመካበት ነበረው፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት መመካት አይችልም። መጽሐፍስ ምን ይላል? “አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት።” አንድ ሰው ሥራ ከሠራ ደመወዙ እንደ ስጦታ ሳይሆን እንደ ተገቢ ዋጋው ይቈጠርለታል። ነገር ግን ለማይሠራ፣ ሆኖም ኀጥኡን በሚያጸድቀው ለሚያምን፣ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቈጠርለታል። ዳዊትም እግዚአብሔር ጽድቅን ያለ ሥራ ስለሚቈጥርለት ሰው ብፅዕና እንዲህ ብሏል፤ “መተላለፋቸው ይቅር የተባለላቸው፣ ኀጢአታቸው የተሰረየላቸው፣ ብፁዓን ናቸው። ኀጢአቱን፣ ጌታ ከቶ የማይቈጥርበት ሰው ምስጉን ነው።” ይህ ብፅዕና ለተገረዙት ብቻ ነው ወይስ ላልተገረዙትም? የአብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት ብለናል። ታዲያ እንዴት ተቈጠረለት? ከተገረዘ በኋላ ነው ወይስ ከመገረዙ በፊት? የተቈጠረለት ከተገረዘ በኋላ ሳይሆን ከመገረዙ በፊት ነው። ሳይገረዝ በነበረው እምነት ላገኘው ጽድቅ፣ የመገረዝን ምልክት ይኸውም የጽድቅን ማኅተም ተቀበለ፤ ስለዚህ ለሚያምኑ ነገር ግን ላልተገረዙት ጽድቅ ይቈጠርላቸው ዘንድ የሁሉ አባት ነው። እርሱ ለተገረዙትም አባት ነው፤ መገረዝ ብቻ ሳይሆን፣ አባታችን አብርሃም ከመገረዙ በፊት የነበረውን የእምነቱን ፈለግ ለሚከተሉ ሁሉ ነው።

ሮሜ 4:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እንግዲህ በሥጋ አባታችን የሆነ አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢሆን የሚመካበት አለውና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘንድ አይደለም። መጽሐፍስ ምን አለ? አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቍኦጠረለት። ለሚሠራ ደመወዝ እንደ ዕዳ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቍኦጠርለትም፤ ነገር ግን ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያደድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል። እንደዚህ ዳዊት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ሥራ ጽድቅን ስለሚቆጥርለት ስለ ሰው ብፅዕና ይናገራል እንዲህ ሲል፦ ዓመፃቸው የተሰረየላቸው ኃጢአታቸውም የተከደነላቸው ብፁዓን ናቸው፤ ጌታ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብፁዕ ነው። እንግዲህ ይህ ብፅዕና ስለ መገረዝ ተነገረ? ወይስ ደግሞ ስለ አለመገረዝ? እምነቱ ለአብርሃም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት እንላለንና። እንዴት ተቆጠረለት? ተገርዞ ሳለ ነውን? ወይስ ሳይገረዝ? ተገርዞስ አይደለም፥ ሳይገረዝ ነበር እንጂ። ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘው የጽድቅ ማኅተም የሆነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ፤ ይህም እነርሱ ደግሞ ጻድቃን ሆነው ይቆጠሩ ዘንድ ሳይገረዙ ለሚያምኑ ሁሉ አባት እንዲሆን ነው፥ ለተገረዙትም አባት እንዲሆን ነው፤ ይኸውም ለተገረዙት ብቻ አይደለም ነገር ግን አባታችን አብርሃም ሳይገረዝ የነበረውን የእምነቱን ፍለጋ ደግሞ ለሚከተሉ ነው።

ሮሜ 4:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እንግዲህ በሥጋ አባታችን የሆነ አብርሃም አገኘ የምንለው ምንድን ነው? አብርሃም የጸደቀው በሥራ ቢሆን ኖሮ፥ የሚመካበት ነገር ባገኘ ነበር፤ ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር ፊት መመካት አይችልም። ቅዱስ መጽሐፍ “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” ይላል። የሚሠራ ሰው የሚያገኘው ደመወዝ ተገቢ የጒልበቱን ዋጋ ነው እንጂ ስጦታ አይደለም። ሰው መልካም ሥራ ባይኖረው እንኳ ኃጢአተኞችን በሚያጸድቅ አምላክ ካመነ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቈጠርለታል። ዳዊትም በበኩሉ እግዚአብሔር ያለ መልካም ሥራ የሚያጸድቀው ሰው ምን ያኽል የተባረከ መሆኑን ሲገልጥ እንዲህ ብሎአል፦ “በደላቸው ይቅር የተባለላቸውና ኃጢአታቸው የተደመሰሰላቸው ሰዎች የተባረኩ ናቸው! ጌታ ኃጢአቱን የማይቈጥርበት ሰው የተባረከ ነው!” ታዲያ፥ ዳዊት የተናገረው ይህ በረከት ለተገረዙት ብቻ ነውን? ወይስ ላልተገረዙትም? ላልተገረዙትም ነው፤ “አብርሃም በእግዚአብሔር ስላመነ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” ብለናል። እንግዲህ አብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ የተቈጠረለት መቼ ነው? ከመገረዙ በፊት ነውን ወይስ ከተገረዘ በኋላ? ከመገረዙ በፊት ነው እንጂ ከተገረዘ በኋላ አይደለም። አብርሃም ገና ከመገረዙ በፊት እምነቱ ጽድቅ ሆኖ እንደ ተቈጠረለት ማረጋገጫ ምልክት እንዲሆነው ተገረዘ፤ ስለዚህ አብርሃም፥ ሳይገረዙ ለሚያምኑና እምነታቸው ጽድቅ ሆኖ ለሚቈጠርላቸው ሁሉ አባት ነው። እንዲሁም አብርሃም ለተገረዙትም አባት ነው፤ ለተገረዙት አባት የሆነበትም ምክንያት በመገረዛቸው ብቻ ሳይሆን እርሱ ከመገረዙ በፊት የነበረውን እምነት በመከተላቸውም ጭምር ነው።

ሮሜ 4:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እንግዲህ በሥጋ አባታችን የሆነ አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢሆን የሚመካበት አለውና፤ በእግዚአብሔር ፊት ግን መመካት አይችልም። መጽሐፉስ ምን አለና? “አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት።” እንግዲህ ለሚሠራ ሰው፥ ደመወዝ እንደ ክፍያ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቆጠርለትም፤ ለማይሠራ፥ ነገር ግን ኃጢአተኛውን በሚያጸድቅ ለሚያምን፥ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል። ደግሞም ዳዊት እንኳ፥ እግዚአብሔር ያለ ሥራ፥ ጽድቅን ስለሚቆጥርለት ሰው፥ ስለ መባረኩ ሲናገር፤ “መተላለፋቸው ይቅር የተባለላቸው፥ ኃጢአታቸውም የተከደነላቸው የተባረኩ ናቸው፤ ጌታ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው የተባረከ ነው።” እንግዲህ ይህ መባረክ በመገረዝ መጣን? ወይስ ደግሞ ባለመገረዝ? አብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት እንላለንና። እንዴት ታዲያ ተቆጠረለት? ተገርዞ ሳለ ነውን? ወይስ ሳይገረዝ? ሳይገረዝ ነበር እንጂ፤ ከተገረዘ በኋላ አይደለም። ሳይገረዝም በእምነቱ ባገኘው የጽድቅ ማኅተም፥ መገረዝን እንደ ምልክት ተቀበለ፤ ሳይገረዙ ለሚያምኑ ሁሉ፥ ለእነርሱም ጽድቅ ሆኖ እንዲቆጠርላቸው አባት ነውና፤ ለተገረዙትም አባት ነው፤ ለተገረዙት ብቻ ሳይሆን፥ ነገር ግን አባታችን አብርሃም ከመገረዙ በፊት የነበረውን የእምነቱን ፈለግ ለሚከተሉ ጭምር ነው።