ሮሜ 3:1-23

ሮሜ 3:1-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እን​ግ​ዲህ አይ​ሁ​ዳዊ የመ​ባል ትርፉ ምን​ድን ነው? የግ​ዝ​ረ​ትስ ጥቅ​ምዋ ምን​ድን ነው? በሁሉ ነገር ብዙ ነው፤ ነገር ግን ከዚያ አስ​ቀ​ድሞ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል አደራ ተሰ​ጣ​ቸው። የማ​ያ​ምኑ ቢኖ​ሩስ የእ​ነ​ርሱ አለ​ማ​መን ሌላ​ውን በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዳ​ያ​ምን ይከ​ለ​ክ​ላ​ልን? አይ​ከ​ለ​ክ​ልም። መጽ​ሐፍ፥ “በነ​ገ​ርህ ትጸ​ድቅ ዘንድ፥ በፍ​ር​ድ​ህም ታሸ​ንፍ ዘንድ” ብሎ እንደ ተና​ገረ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እው​ነ​ተና ነውና፥ ሰውም ሁሉ ሐሰ​ተና ነውና። በእኔ ኀጢ​አት የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጽድቅ ከጸና እን​ግ​ዲህ ምን እን​ላ​ለን? እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በሰው ላይ ቅጣ​ትን ቢያ​መጣ ይበ​ድ​ላ​ልን? አይ​በ​ድ​ልም፤ የም​ና​ገ​ረ​ው​ንም በሰው ልማድ እና​ገ​ራ​ለሁ። እን​ዲ​ህማ ከሆነ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በዓ​ለም እን​ደ​ምን ይፈ​ር​ዳል? የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እው​ነት በእኔ ሐሰ​ተ​ና​ነት ለክ​ብሩ ከፍ ከአለ እን​ግ​ዲህ እኔን እንደ ኀጢ​አ​ተና ለምን ይፈ​ር​ድ​ብ​ናል? በውኑ እና መል​ካም ነገር እና​ገኝ ዘንድ ክፉ ነገር እና​ድ​ርግ እን​ደ​ም​ንል አስ​መ​ስ​ለው የሚ​ጠ​ረ​ጥ​ሩ​ንና የሚ​ነ​ቅ​ፉን ሰዎች እን​ደ​ሚ​ሰ​ድ​ቡን ነን? ለእ​ነ​ር​ሱስ ቅጣ​ታ​ቸው ተዘ​ጋ​ጅ​ቶ​ላ​ቸ​ዋል። እን​ግ​ዲህ ምን እን​ላ​ለን? ከእ​ነ​ርሱ እን​በ​ል​ጣ​ለን? አይ​ደ​ለም፤ አይ​ሁ​ዳ​ዊ​ንም፥ አረ​ማ​ዊ​ንም እነሆ፥ አስ​ቀ​ድ​መን ነቅ​ፈ​ና​ቸ​ዋል፤ ሁሉም ስተ​ዋ​ልና። መጽ​ሐፍ እን​ዲህ እን​ዳለ “አንድ ስንኳ ጻድቅ የለም። አስ​ተ​ዋ​ይም የለም፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም የሚ​ሻው የለም። ሁሉም ተባ​ብሮ በደለ፤ በጎ ሥራ​ንም የሚ​ሠራ የለም፤ አንድ ስንኳ ቢሆን የለም። ጕረ​ሮ​አ​ቸው እንደ ተከ​ፈተ መቃ​ብር ነው፤ በአ​ን​ደ​በ​ታ​ቸ​ውም ሸነ​ገሉ፤ ከከ​ን​ፈ​ሮ​ቻ​ቸ​ውም በታች የእ​ባብ መርዝ አለ፤ አፋ​ቸው መራራ ነው፤ መር​ገ​ም​ንም የተ​ሞላ ነው። እግ​ሮ​ቻ​ቸ​ውም ደምን ለማ​ፍ​ሰስ ፈጣ​ኖች ናቸው። በመ​ን​ገ​ዳ​ቸው ጥፋ​ትና ጕስ​ቍ​ልና አለ። የሰ​ላ​ምን መን​ገድ አያ​ው​ቋ​ትም። በዐ​ይ​ኖ​ቻ​ቸ​ውም ፊት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መፍ​ራት የለም።” አን​ደ​በት ሁሉ ይዘጋ ዘንድ፥ ዓለ​ምም ሁሉ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ኦሪት የሚ​ና​ገ​ረው ሁሉ በኦ​ሪት ላሉት እንደ ተነ​ገረ እና​ው​ቃ​ለን። ከኦ​ሪት የተ​ነሣ ኀጢ​አት ስለ ታወ​ቀች ሰው ሁሉ የኦ​ሪ​ትን ሥር​ዐት በመ​ፈ​ጸም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት አይ​ጸ​ድ​ቅም። አሁን ግን በኦ​ሪ​ትና በነ​ቢ​ያት የተ​መ​ሰ​ከ​ረ​ላት የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጽድቅ ያለ ኦሪት ተገ​ለ​ጠች። የሚ​ያ​ም​ኑ​በት ሁሉ ኢየ​ሱስ ክር​ስ​ቶ​ስን በማ​መን በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ይጸ​ድ​ቃሉ። በዚ​ህም ልዩ​ነት የለም፤ ሁሉም ፈጽ​መው በድ​ለ​ዋ​ልና፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ማክ​በ​ር​ንም ትተ​ዋ​ልና።

ሮሜ 3:1-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ታዲያ አይሁዳዊ መሆን ጥቅሙ ምንድን ነው? መገረዝስ ምን ፋይዳ አለው? በየትኛውም መንገድ ጥቅሙ ብዙ ነው፤ ከሁሉ አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃል በዐደራ የተሰጠው ለእነርሱ ነው። አንዳንዶች እምነት ባይኖራቸውስ? የእነርሱ አለማመን የእግዚአብሔርን ታማኝነት ዋጋ ያሳጣዋልን? ከቶ አይሆንም! ይልቅስ እግዚአብሔር እውነተኛ፣ ሰው ሁሉ ግን ሐሰተኛ ይሁን፤ “በቃልህ ትጸድቅ፣ በፍርድም ፊት ረቺ ትሆን ዘንድ” ተብሎ ተጽፏልና። የእኛ ዐመፃ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አጕልቶ የሚያሳይ ከሆነ፣ ምን ማለት እንችላለን? እንደ ሰው ለመከራከር ያህል እግዚአብሔር በእኛ ላይ ቍጣውን በማምጣቱ ዐመፀኛ ነውን? እንደ ሰው ሲታሰብ ማለቴ ነው። ከቶ አይሆንም! እንዲህ ቢሆንማ ኖሮ እግዚአብሔር በዓለም ላይ እንዴት ሊፈርድ ይችላል? “የእኔ ውሸተኛ መሆን የእግዚአብሔርን እውነተኛነት የሚያጐላ፣ ክብሩንም የሚጨምርለት ከሆነ፣ ኀጢአተኛ ተብዬ እስካሁን እንዴት ይፈረድብኛል?” በማለት ሊከራከር የሚችል ሰው ይኖር ይሆናል። ይህማ “በጎ እንዲመጣ ክፉ እንሥራ” ይላሉ በማለት አንዳንዶች እንደሚያስወሩብን ነው፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ፍርድ ትክክለኛ ነው። እንግዲህ ምን እንላለን? እኛ ከእነርሱ እንበልጣለንን? ከቶ አይደለም፤ አይሁድም ሆኑ አሕዛብ፣ ሁሉም ከኀጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከስሰናቸዋል። እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ “ጻድቅ ማንም የለም፤ አንድ እንኳ፤ አስተዋይ የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚሻ አንድም የለም። ሁሉም ተሳስተዋል፤ በአንድነት የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ መልካም የሚያደርግ የለም፤ አንድ እንኳ።” “ጕረሯቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ይሸነግላሉ።” “በከንፈሮቻቸው የእባብ መርዝ አለ።” “አፋቸው ርግማንና ምሬት ሞልቶበታል።” “እግሮቻቸው ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፤ በመንገዶቻቸው ጥፋትና ጕስቍልና ይገኛሉ፤ የሰላምንም መንገድ አያውቁም።” “በዐይናቸው ፊት ፈሪሀ እግዚአብሔር የለም።” እንግዲህ አፍ ሁሉ እንዲዘጋና ዓለም በሙሉ ለእግዚአብሔር መልስ እንዲሰጥ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደ ሆነ፣ እናውቃለን፤ ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ማንም ሥጋ ለባሽ በርሱ ፊት ሊጸድቅ አይችልም፤ ይልቁንም በሕግ አማካይነት ኀጢአትን እንገነዘባለን። አሁን ግን ሕግና ነቢያት የመሰከሩለት፣ ከሕግ ውጭ የሆነ፣ የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጧል። ይህ የእግዚአብሔር ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን የሚገኝ ጽድቅ ነው። ልዩነት የለም፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሏቸዋል፤

ሮሜ 3:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እንግዲህ የአይሁዳዊ ብልጫው ምንድር ነው? ወይስ የመገረዝ ጥቅሙ ምንድር ነው? በሁሉ ነገር ብዙ ነው። አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃላት አደራ ተሰጡአቸው። ታዲያ ምንድር ነው? የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን? እንዲህ አይሁን፤ በቃልህ ትጸድቅ ዘንድ ወደ ፍርድ በገባህም ጊዜ ትረታ ዘንድ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ሰው ሁሉ ውሸተኛ ከሆነ እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን። ነገር ግን ዓመፃችን የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሚያስረዳ ከሆነ ምን እንላለን? ቍጣን የሚያመጣ እግዚአብሔር ዓመፀኛ ነውን? እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። እንዲህ አይሁን፤ እንዲህ ቢሆን እግዚአብሔር በዓለም እንዴት ይፈርዳል? በእኔ ውሸት ግን የእግዚአብሔር እውነት ለክብሩ ከላቀ ስለምን በእኔ ደግሞ እንደ ኃጢአተኛ ገና ይፈርድብኛል? ስለ ምንስ መልካም እንዲመጣ ክፉ አናደርግም? እንዲሁ ይሰድቡናልና አንዳንዱም እንዲሁ እንድንል ይናገራሉና። የእነርሱም ፍርድ ቅን ነው። እንግዲህ ምን ይሁን? ከእነርሱ እንበልጣለንን? ከቶ አይደለም፤ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋልና፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም። ጕሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤ እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፥ የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም። አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን፤ ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና። አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥ እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤

ሮሜ 3:1-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እንግዲህ አይሁዳዊ ከአሕዛብ የሚበልጠው በምንድን ነው? የመገረዝስ ጥቅሙ ምንድን ነው? በእርግጥ አይሁዳዊ መሆን በብዙ መንገድ ብልጫ አለው፤ ዋናው ነገር እግዚአብሔር ቃሉን ለአይሁድ ዐደራ መስጠቱ ነው። ታዲያ፥ ከአይሁድ አንዳንዶቹ ታማኞች ሆነው ባይገኙ፥ የእነርሱ ታማኞች አለመሆን የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን? ከቶ አያስቀርም! “ከቃልህ የተነሣ እውነተኛ ትሆናለህ፤ ባላጋራህንም በፍርድ ትረታለህ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ቢሆንም እግዚአብሔር እውነተኛ ነው። ነገር ግን የእኛ ኃጢአት የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሚያሳይ ከሆነ እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ስለ ኃጢአታችን ቢቀጣን ትክክለኛ ፈራጅ አይደለም ማለት ነውን? እዚህ ላይ የምናገረው እንደ ሰው አስተሳሰብ ነው። ፈጽሞ አይደለም! እንዲህ ከሆነማ እግዚአብሔር በዓለም ላይ እንዴት ይፈርዳል? ነገር ግን የእኔ ሐሰተኛነት የእግዚአብሔርን እውነት በመግለጥ፥ የክብሩን ብዛት የሚያሳይ ከሆነ ታዲያ፥ እኔ እንደ ኃጢአተኛ የሚፈረድብኝ ስለ ምንድን ነው? አንዳንድ ሰዎች “መልካም ነገር እንድናገኝ ክፉ ነገር እናድርግ” እያልኩ የማስተምር አስመስለው ይከሱኛል፤ ስለዚህ እንዲህ ባሉት ላይ የሚፈረድባቸው ፍርድ ትክክለኛ ነው። ታዲያ፥ እኛ አይሁድ ከአሕዛብ እንበልጣለን ማለት ነውን? ከቶ አይደለም! ሰዎች ሁሉ አይሁድም ሆኑ አሕዛብ ኃጢአተኞች መሆናቸውን ቀደም ብዬ አስረድቻለሁ። እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ “አንድ እንኳ ጻድቅ ሰው የለም፤ አንድ እንኳን የለም፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ አንድም የለም። ሁሉም ከመንገድ ወጥተዋል፤ በአንድነት ሆነው ተሳስተዋል። ደግ ሥራ የሚሠራ አንድ ሰው እንኳ የለም። ሰውን የሚጐዳ ክፉ ቃል ለመናገር አፋቸው እንደ መቃብር የተከፈተ ነው፤ በምላሳቸው ያታልላሉ፤ የከንፈራቸውም ንግግር እንደ እባብ መርዝ የሚጐዳ ነው፤ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል። እግራቸው ሰውን ለመግደል የፈጠነ ነው፤ በመንገዳቸው የሚገኘው ጥፋትና ጒስቊልና ነው። የሰላምን መንገድ አያውቁም፤ እግዚአብሔርን ከቶ አይፈሩም።” የሕግ ትእዛዝ የሚመለከተው ከሕግ በታች ያሉትን እንደ ሆነ እናውቃለን፤ በዚህ ምክንያት ሰዎች የሚያመካኙት አጥተው ዝም ይላሉ፤ ዓለሙም ሁሉ በእግዚአብሔር ፍርድ ሥር ይሆናል። ስለዚህ ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት፥ ሕግን በመፈጸም አይጸድቅም፤ ሕግ የሚያሳየው ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ መሆኑን ነው። አሁን ግን እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያጸድቅበት መንገድ ያለ ሕግ መሆኑ ተገልጦአል፤ ይህም በሙሴ ሕግና በነቢያት ተመስክሮአል። ስለዚህ እግዚአብሔር ምንም ልዩነት ሳያደርግ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ ጽድቅን ይሰጣል። ሰዎች ሁሉ ኃጢአት ሠርተዋል፤ እግዚአብሔር የሰጣቸውንም ክብር አጥተዋል።

ሮሜ 3:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እንግዲህ አይሁዳዊው ጥቅሙ ምንድነው? ወይም የመገረዝ ትርፉ ምንድነው? በማንኛውም መንገድ ጥቅሙ ብዙ ነው። አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃላት አደራ ተሰጣቸው። አንዳንዶች ባያምኑስ? የእነሱ አለማመን የእግዚአብሔርን ታማኝነት ዋጋ የሌለው ያደርገዋልን? በጭራሽ! “በቃልህ እውነተኛ እንድትሆን፥ ለፍርድ በቀረብክም ጊዜ አሸናፊ እንድትሆን፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ግን እውነተኛ ይሁን። ነገር ግን ዐመፃችን የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሚያጎላ ከሆነ ምን እንላለን? እግዚአብሔር በቁጣ ቢቀጣን ትክክል አይደለም ሊባል ነውን? እንደ ሰው እላለሁ። በጭራሽ! ያለበለዚያ እግዚአብሔር ዓለምን እንዴት ይፈርዳል? ነገር ግን የእግዚአብሔር እውነተኛነት በእኔ ውሸት ለክብሩ ከሞላ፥ ለምን እኔ እስካሁን እንደ ኃጢአተኛ ይፈረድብኛል? “መልካም ነገር እንዲመጣ ለምን ክፉ አናደርግም?” ይላሉ ብለው እንደሚያሙን አይደለም፤ የሚፈረድባቸው ፍርድ ትክክለኛ ነው። ስለዚህ ምን ይሁን? እኛ እንበልጣለንን? በጭራሽ! አይሁዳውያንንም ግሪካውያንንም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ “ጻድቅ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም፤ የሚያስተውል የለም፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ የለም፤ ሁሉም ከመንገድ ወጥተዋል፤ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ መልካም የሚሠራ አንድም የለም፤ አንድ ስንኳ የለም።” “ጉሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸውም አታለዋል፤” “የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤” “አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቷል፤” “እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፤ የሰላምንም መንገድ አያውቁም።” “በዐይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም።” ነገር ግን አፍ ሁሉ እንዲዘጋና ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ ሥር እንዲሆን፤ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደሚናገር እናውቃለን፤ ምክንያቱም በሕግ ሥራ ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት አይጸድቅም፤ በሕግ አማካኝነት ኃጢአት ይታወቃልና። አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፤ ይህ የእግዚአብሔር ጽድቅ ለሚያምኑ ሁሉ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እምነት የሚገኝ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ ሁሉም ኃጢአትን ሠርተዋልና፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤