ሮሜ 2:3-8
ሮሜ 2:3-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አንተ ሰው ሆይ፥ በሌላ ላይ አይተህ የምትጠላውንና የምትነቅፈውን ያን አንተ ራስህ የምትሠራው ከሆነ፥ ከእግዚአብሔር ፍርድ እንደምታመልጥ ታስባለህን? ወይስ በቸርነቱ ብዛት በመታገሡ፥ ለአንተም እሺ በማለቱ እግዚአብሔርን አላዋቂ ልታደርገው ታስባለህን? የእግዚአብሔርስ ቸርነቱ አንተን ወደ ንስሓ እንዲመልስህ አታውቅምን? ነገር ግን ልቡናህን እንደ ማጽናትህ፥ ንስሓም እንደ አለመግባትህ መጠን የእግዚአብሔር እውነተና ፍርድ በሚገለጥበት ቀን መቅሠፍትን ለራስህ ታከማቻለህ። እርሱ በእውነተና ፍርዱ ለሁሉ እንደ ሥራው ይከፍለዋልና። በበጎ ምግባር ጸንተው ለሚታገሡ፥ ምስጋናና ክብርን፥ የማይጠፋ ሕይወትንም ለሚሹ እርሱ የዘለዓለም ሕይወትን ይሰጣቸዋል። ለሚክዱና እውነትን ለሚለውጡ፥ ዐመፅንም ለሚወድዱ ሰዎች ዋጋቸው ቍጣና መቅሠፍት ነው።
ሮሜ 2:3-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ አንተ ሰው በሌሎች ላይ እየፈረድህ ያንኑ የምታደርግ ከሆነ፣ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃል? ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሓ የሚመራህ መሆኑን ሳትገነዘብ፣ የቸርነቱን፣ የቻይነቱንና የትዕግሥቱን ባለጠግነት ትንቃለህ? ነገር ግን በድንዳኔህና ንስሓ በማይገባ ልብህ ምክንያት ትክክለኛ ፍርዱ ሲገለጥ በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን በራስህ ላይ ቍጣን ታከማቻለህ። እግዚአብሔር “ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይሰጠዋል”። በጎ የሆነውን ጸንቶ በማድረግ ክብርን፣ ሞገስንና ዘላለማዊነትን ለሚሹ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል። ነገር ግን በራስ ወዳዶች፣ እውነትን ትተው ክፋትን በሚከተሉ ፍርድና ቍጣ ይደርስባቸዋል።
ሮሜ 2:3-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ የምትፈርድ ያንም የምታደርግ ሰው ሆይ፥ አንተ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን? ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ። እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤ በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቍጣና መቅሠፍት ይሆንባቸዋል።
ሮሜ 2:3-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንተ ሰው! እንዲህ በሚያደርጉት ሰዎች ላይ እየፈረድክ፥ እነርሱ የሚያደርጉትን ስታደርግ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን? ወይስ የእግዚአብሔርን የደግነቱንና የቻይነቱን፥ የታጋሽነቱንም ብዛት ትንቃለህን? እግዚአብሔር ደግነቱን ያበዛልህ አንተን ወደ ንስሓ ለመምራት እንደ ሆነ አታውቅምን? እንግዲህ አንተ ንስሓ ባለመግባትህና እልኸኛ በመሆንህ የእግዚአብሔር ቊጣና ትክክለኛ ፍርድ በሚገለጥበት ቀን ቅጣትህ እንዲበዛ ታደርጋለህ። እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ እንደየሥራው ይሰጠዋል። በመልካም ሥራ በመጽናት ምስጋናና ክብርን የማይጠፋ ሕይወትንም ለሚፈልጉ እግዚአብሔር የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል። የራሳቸውን ጥቅም በሚፈልጉ፥ ለእውነት በማይታዘዙና ለዐመፅ በሚታዘዙ ዐድመኞች ላይ ግን የእግዚአብሔር ቊጣና መቅሠፍት ይመጣባቸዋል።
ሮሜ 2:3-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ ላይ የምትፈርድ ያንንም የምታደርግ ሰው ሆይ! ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን? ወይስ የቸርነቱን፥ የቻይነቱን፥ የታጋሽነቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሓ ሊመራህ እንደሆነ አታውቅምን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሓ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቁጣ ቀን በራስህ ላይ ቁጣን ታከማቻለህ። እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይሰጠዋል፤ በመልካም ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ በራስ ወዳዶች፥ ለእውነት በማይታዘዙት ነገር ግን ለዐመፃ በሚታዘዙት ላይ ቁጣና መቅሠፍት ይመጣባቸዋል።