ሮሜ 2:1-4
ሮሜ 2:1-4 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አንተ ሰው ሆይ፥ እውነት ለሚፈርደው ለእግዚአብሔር ምን ትመልስለታለህ? በወንድምህ ላይ የምትጠላውን ያን ሥራ አንተ ራስህ ከሠራኸው በራስህ የምትፈርድ አይደለምን? አንተ ራስህ ያን ሥራ ትሠራዋለህና። ይህም እንደዚህ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ቅጣት የሚያመጣ የእግዚአብሔር ፍርዱ እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን። አንተ ሰው ሆይ፥ በሌላ ላይ አይተህ የምትጠላውንና የምትነቅፈውን ያን አንተ ራስህ የምትሠራው ከሆነ፥ ከእግዚአብሔር ፍርድ እንደምታመልጥ ታስባለህን? ወይስ በቸርነቱ ብዛት በመታገሡ፥ ለአንተም እሺ በማለቱ እግዚአብሔርን አላዋቂ ልታደርገው ታስባለህን? የእግዚአብሔርስ ቸርነቱ አንተን ወደ ንስሓ እንዲመልስህ አታውቅምን?
ሮሜ 2:1-4 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ አንተ በሌላው ላይ የምትፈርድ፣ የምታመካኝበት የለህም፤ በሌላው ላይ በምትፈርድበት ነገር ሁሉ፣ ራስህን ትኰንናለህ፤ ፈራጅ የሆንኸው አንተ ያንኑ ታደርጋለህና። እንደዚህ በሚያደርጉትም ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ መሆኑን እናውቃለን። እንግዲህ አንተ ሰው በሌሎች ላይ እየፈረድህ ያንኑ የምታደርግ ከሆነ፣ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃል? ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሓ የሚመራህ መሆኑን ሳትገነዘብ፣ የቸርነቱን፣ የቻይነቱንና የትዕግሥቱን ባለጠግነት ትንቃለህ?
ሮሜ 2:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ፥ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፥ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኰንናለህና፤ አንተው ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና። እንደዚህም በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደ ሆነ እናውቃለን። አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ የምትፈርድ ያንም የምታደርግ ሰው ሆይ፥ አንተ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን? ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?
ሮሜ 2:1-4 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በሌላው ሰው ላይ የምትፈርድ አንተ ለራስህ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው ሰው ላይ ስትፈርድ በራስህ ላይ ትፈርዳለህ፤ አንተ በሰው ላይ እየፈረድክ፥ ያ የፈረድክበት ሰው የሚያደርገውን ታደርጋለህ። ይህን በሚያደርጉ ሰዎች ላይ፥ እግዚአብሔር የሚገባቸውን እንደሚፈርድባቸው እናውቃለን። አንተ ሰው! እንዲህ በሚያደርጉት ሰዎች ላይ እየፈረድክ፥ እነርሱ የሚያደርጉትን ስታደርግ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን? ወይስ የእግዚአብሔርን የደግነቱንና የቻይነቱን፥ የታጋሽነቱንም ብዛት ትንቃለህን? እግዚአብሔር ደግነቱን ያበዛልህ አንተን ወደ ንስሓ ለመምራት እንደ ሆነ አታውቅምን?
ሮሜ 2:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ አንተ የምትፈርድ ሰው ሆይ! የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው ላይ በምትፈርድበት ነገር በራስህ ላይ ትፈርዳለህ፤ ፈራጅ የሆንከው አንተ ያንኑ ታደርጋለህና። እንደዚህ በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደሆነ እናውቃለን። አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ ላይ የምትፈርድ ያንንም የምታደርግ ሰው ሆይ! ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን? ወይስ የቸርነቱን፥ የቻይነቱን፥ የታጋሽነቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሓ ሊመራህ እንደሆነ አታውቅምን?