ሮሜ 14:6-9
ሮሜ 14:6-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አንዳንድ ቀን የተከለከለም ለእግዚአብሔር ተከለከለ፤ ዘወትር የተከለከለም ለእግዚአብሔር ተከለከለ፤ የበላም ለእግዚአብሔር በላ፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግነዋል፤ ያልበላም ለእግዚአብሔር አልበላም፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግነዋል። ከመካከላችንም ለራሱ የሚኖር፥ ለራሱም የሚሞት የለም። በሕይወት ብንኖርም ለእግዚአብሔር እንኖራለን፤ ብንሞትም ለእግዚአብሔር እንሞታለን፤ እንግዲህ በሕይወት ብንኖርም ብንሞትም ለእግዚአብሔር ነን። ስለዚህ ሕያዋንንና ሙታንን ይገዛ ዘንድ ክርስቶስ ሞተ፥ ተነሣም።
ሮሜ 14:6-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንድን ቀን ከሌላው የተለየ አድርጎ የሚያስብ ሰው፣ እንዲህ የሚያደርገው ለጌታ ብሎ ነው፤ ሥጋ የሚበላውም ለጌታ ብሎ ይበላል፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባልና። የማይበላም ለጌታ ሲል አይበላም፤ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ያቀርባል። ከእኛ ማንም ለራሱ የሚኖር፣ ለራሱም የሚሞት የለምና። ብንኖር ለጌታ እንኖራለን፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። ስለዚህ ብንኖርም ብንሞትም የጌታ ነን። ለዚሁ፣ የሙታንና የሕያዋን ጌታ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ ሞቷል፤ በሕይወትም ተነሥቷል።
ሮሜ 14:6-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ቀንን የሚያከብር ለጌታ ብሎ ያከብራል፤ የሚበላም እግዚአብሔርን ያመሰግናልና ለጌታ ብሎ ይበላል፤ የማይበላም ለጌታ ብሎ አይበላም እግዚአብሔርንም ያመሰግናል። ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፥ ለራሱም የሚሞት የለም፤ በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን። ስለዚህ ነገር ሙታንንም ሕያዋንንም ይገዛ ዘንድ ክርስቶስ ሞቶአልና ሕያውም ሆኖአልና።
ሮሜ 14:6-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንዱን ቀን ከሌላው ቀን አስበልጦ የሚያከብር ቢኖር ይህን ማድረጉ ለጌታ ክብር ብሎ ነው፤ ማንኛውንም ምግብ የሚበላ ለጌታ ክብር ብሎ ይበላል፤ ስለሚበላውም ምግብ እግዚአብሔርን ያመሰግናል፤ ማንኛውንም ምግብ የማይበላ ለጌታ ክብር ብሎ አይበላም፤ ባለመብላቱም እግዚአብሔርን ያመሰግናል። ከእኛ እያንዳንዱ ሕይወቱም ሆነ ሞቱ የራሱ አይደለም። ብንኖር ለጌታ እንኖራለን፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን፤ ስለዚህ ብንኖርም፥ ብንሞትም የጌታ ነን። ስለዚህ ክርስቶስ ሞቶ ከሞት የተነሣው የሕያዋንና የሙታን ጌታ ለመሆን ነው።
ሮሜ 14:6-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አንድን ቀን ከሌላው የተለየ አድርጎ የሚያስብ ሰው ለጌታ ብሎ ነው፤ የሚበላም ለጌታ ብሎ ይበላል፤ እግዚአብሔርን ያመሰግናልና የማይበላም ለጌታ ብሎ አይበላም፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግናል። ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፤ ለራሱም የሚሞት የለም፤ በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን። ስለዚህ ነገር የሙታንንና የሕያዋን ጌታ እንዲሆን ክርስቶስ ሞቷልና፥ ሕያውም ሆኖአልና።