ሮሜ 14:5-12
ሮሜ 14:5-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከቀን ቀን የሚከለከል አለና፤ ዘወትርም የሚከለከል አለና፤ ነገር ግን ሁሉም ልቡ እንደ ወደደ ያድርግ። አንዳንድ ቀን የተከለከለም ለእግዚአብሔር ተከለከለ፤ ዘወትር የተከለከለም ለእግዚአብሔር ተከለከለ፤ የበላም ለእግዚአብሔር በላ፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግነዋል፤ ያልበላም ለእግዚአብሔር አልበላም፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግነዋል። ከመካከላችንም ለራሱ የሚኖር፥ ለራሱም የሚሞት የለም። በሕይወት ብንኖርም ለእግዚአብሔር እንኖራለን፤ ብንሞትም ለእግዚአብሔር እንሞታለን፤ እንግዲህ በሕይወት ብንኖርም ብንሞትም ለእግዚአብሔር ነን። ስለዚህ ሕያዋንንና ሙታንን ይገዛ ዘንድ ክርስቶስ ሞተ፥ ተነሣም። እንግዲህ በወንድምህ ላይ የምትፈርድ አንተ ምንድን ነህ? ወንድምህንስ የምትነቅፍ አንተ ምንድን ነህ? ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት እንቆማለንና። እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአልና፥ “እኔ ሕያው ነኝ፤ ጕልበትም ሁሉ ለእኔ ይሰግዳል፤ አንደበትም ሁሉ ለእኔ ይገዛል።” እነሆ፥ ሁላችን በእግዚአብሔር ዘንድ እንደምንመረመር ታወቀ።
ሮሜ 14:5-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንድ ሰው አንዱን ቀን ከሌላው የተሻለ ቅዱስ አድርጎ ይቈጥራል፤ ሌላው ደግሞ ቀኖች ሁሉ እኩል እንደ ሆኑ ያስባል። እያንዳንዱ የራሱን ውሳኔ ልብ ብሎ ይወስን። አንድን ቀን ከሌላው የተለየ አድርጎ የሚያስብ ሰው፣ እንዲህ የሚያደርገው ለጌታ ብሎ ነው፤ ሥጋ የሚበላውም ለጌታ ብሎ ይበላል፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባልና። የማይበላም ለጌታ ሲል አይበላም፤ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ያቀርባል። ከእኛ ማንም ለራሱ የሚኖር፣ ለራሱም የሚሞት የለምና። ብንኖር ለጌታ እንኖራለን፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። ስለዚህ ብንኖርም ብንሞትም የጌታ ነን። ለዚሁ፣ የሙታንና የሕያዋን ጌታ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ ሞቷል፤ በሕይወትም ተነሥቷል። ታዲያ አንተ በወንድምህ ላይ ለምን ትፈርዳለህ? ለምንስ ወንድምህን ትንቃለህ? ሁላችንም በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለንና፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ “ ‘እኔ ሕያው ነኝና’ ይላል ጌታ፤ ‘ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር ይመሰክራል።’ ” ስለዚህ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።
ሮሜ 14:5-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይህ ሰው አንድ ቀን ከሌላ ቀን እንዲሻል ያስባል፥ ያ ግን ቀን ሁሉ አንድ እንደ ሆነ ያስባል፤ እያንዳንዱ በገዛ አእምሮው አጥብቆ ይረዳ። ቀንን የሚያከብር ለጌታ ብሎ ያከብራል፤ የሚበላም እግዚአብሔርን ያመሰግናልና ለጌታ ብሎ ይበላል፤ የማይበላም ለጌታ ብሎ አይበላም እግዚአብሔርንም ያመሰግናል። ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፥ ለራሱም የሚሞት የለም፤ በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን። ስለዚህ ነገር ሙታንንም ሕያዋንንም ይገዛ ዘንድ ክርስቶስ ሞቶአልና ሕያውም ሆኖአልና። አንተም በወንድምህ ላይ ስለ ምን ትፈርዳለህ? ወይስ አንተ ደግሞ ወንድምህን ስለ ምን ትንቃለህ? ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና። እኔ ሕያው ነኝ፥ ይላል ጌታ፥ ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል መላስም ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።
ሮሜ 14:5-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንዲሁም አንዱ ቀን ከሌላው ቀን ይበልጥ ክቡር ነው ብሎ የሚያስብ ይኖር ይሆናል፤ ሌላው ደግሞ ቀኖች ሁሉ እኩል ክብር አላቸው እንጂ በቀኖች መካከል ልዩነት የለም ብሎ ያስባል። እንግዲህ ይህን በመሳሰለው ነገር እያንዳንዱ ሰው ከልቡ ያመነበትን ያድርግ። አንዱን ቀን ከሌላው ቀን አስበልጦ የሚያከብር ቢኖር ይህን ማድረጉ ለጌታ ክብር ብሎ ነው፤ ማንኛውንም ምግብ የሚበላ ለጌታ ክብር ብሎ ይበላል፤ ስለሚበላውም ምግብ እግዚአብሔርን ያመሰግናል፤ ማንኛውንም ምግብ የማይበላ ለጌታ ክብር ብሎ አይበላም፤ ባለመብላቱም እግዚአብሔርን ያመሰግናል። ከእኛ እያንዳንዱ ሕይወቱም ሆነ ሞቱ የራሱ አይደለም። ብንኖር ለጌታ እንኖራለን፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን፤ ስለዚህ ብንኖርም፥ ብንሞትም የጌታ ነን። ስለዚህ ክርስቶስ ሞቶ ከሞት የተነሣው የሕያዋንና የሙታን ጌታ ለመሆን ነው። ታዲያ፥ አንተ በወንድምህ ላይ ለምን ትፈርዳለህ? ወይስ ወንድምህን ለምን ትንቀዋለህ? ሁላችንም በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለን። ምክንያቱም፦ “እኔ ሕያው ነኝ ይላል እግዚአብሔር፤ ሰው ሁሉ በጒልበቱ በእኔ ፊት ይንበረከካል፤ በአንደበቱም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ይመሰክራል” ተብሎ ተጽፎአል። ስለዚህ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ሥራ በእግዚአብሔር ፊት ቀርበን መልስ እንሰጣለን።
ሮሜ 14:5-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህ ሰው አንድ ቀን ከሌላ ቀን እንደሚሻል ያስባል፤ ሌላው ግን ቀን ሁሉ አንድ እንደሆነ ያስባል፤ እያንዳንዱ በገዛ አእምሮው አጥብቆ ይረዳ። አንድን ቀን ከሌላው የተለየ አድርጎ የሚያስብ ሰው ለጌታ ብሎ ነው፤ የሚበላም ለጌታ ብሎ ይበላል፤ እግዚአብሔርን ያመሰግናልና የማይበላም ለጌታ ብሎ አይበላም፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግናል። ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፤ ለራሱም የሚሞት የለም፤ በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን። ስለዚህ ነገር የሙታንንና የሕያዋን ጌታ እንዲሆን ክርስቶስ ሞቷልና፥ ሕያውም ሆኖአልና። አንተም በወንድምህ ላይ ስለምን ትፈርዳለህ? ወይስ አንተ ደግሞ ወንድምህን ስለምን ትንቃለህ? ሁላችን በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና። “እኔ ሕያው ነኝ፤” ይላል ጌታ፤ “ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ ልሳንም ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል፤” ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።