ሮሜ 13:7-10
ሮሜ 13:7-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለሁሉም እንደሚገባው አድርጉ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን ስጡ፤ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን ስጡ፤ ዐሥራት ለሚገባው ዐሥራትን ስጡ፤ ሊፈሩት የሚገባውን ፍሩ፤ ክብር የሚገባውንም አክብሩ። እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ባልንጀራውን የወደደ ግን ሕግን ሁሉ ፈጸመ። በኦሪት እንዲህ ብሎአልና፥ “አታመንዝር፤ አትግደል፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፥ አትመኝ፤” ደግሞ ሌላ ትእዛዝ አለ፤ ነገር ግን የሁሉም ራስ “ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው ነው። ባልንጀራዉን የሚወድ በባልንጀራዉ ላይ ክፉ ሥራ አይሠራም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።
ሮሜ 13:7-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ለእያንዳንዱ የሚገባውን ስጡ፤ ግብር ከሆነ ግብርን፣ ቀረጥ ከሆነም ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባውም ክብርን ስጡ። እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር የማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ባልንጀራውን የሚወድድ እርሱ ሕግን ፈጽሟልና። “አታመንዝር”፣ “አትግደል”፣ “አትስረቅ”፣ “አትመኝ” የሚሉትና ሌሎችም ትእዛዞች ቢኖሩም፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” በሚለው በዚህ በአንድ ሕግ ተጠቃልለዋል። ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ መፈጸሚያ ነው።
ሮሜ 13:7-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ። እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፥ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና። አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በውሸት አትመስክር፥ አትመኝ የሚለው ከሌላይቱ ትእዛዝ ሁሉ ጋር በዚህ፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ በሚለው ቃል ተጠቅልሎአል። ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።
ሮሜ 13:7-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ ለበላይ ባለሥልጣን ሊደረግ የሚገባውን ሁሉ አድርጉ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን ክፈሉ፤ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ። የማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ሊኖርባችሁ የሚገባ ዕዳ እርስ በርስ መዋደድ ብቻ ይሁን፤ ሰውን የሚወድ ሕግን ይፈጽማል። “አታመንዝር፤ አትግደል፤ አትስረቅ፤ የሌላ ሰው የሆነውን ማናቸውንም ነገር አትመኝ” የሚሉት ትእዛዞችና ሌሎችም ትእዛዞች ሁሉ “ሰውን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” በሚለው በአንዱ ትእዛዝ ተጠቃለው ይገኛሉ። ሰውን የሚወድ ሁሉ በሚወደው ላይ ክፉ ነገር አያደርግበትም፤ ስለዚህ ሰውን የሚወድ ሕግን ሁሉ ይፈጽማል ማለት ነው።
ሮሜ 13:7-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ለሁሉ የሚገባውን ስጡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ። እርስ በእርሳችሁ ከመዋደድ በቀር የማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሟልና። “አታመንዝር፤ አትግደል፤ አትስረቅ፤ አትመኝ፤” የሚለው እና ሌላም ትእዛዝ ቢኖር፤ በዚህ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤” በሚለው ቃል ተጠቅልሎአል። ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።