ሮሜ 12:1-3
ሮሜ 12:1-3 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞቻችን፥ ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር ሕያውና ቅዱስ፥ ደስ የሚያሰኝም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እማልዳችኋለሁ። ይህም በዕውቀት የሚሆን አገልግሎታችሁ ነው። ይህን ዓለም አትምሰሉ፤ ልባችሁንም አድሱ፤ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካሙንና እውነቱን፥ ፍጹሙንም መርምሩ። በተሰጠኝ በእግዚአብሔር ጸጋ ሁላችሁም እንዳትታበዩ እነግራችኋለሁ፤ ራሳችሁን ከዝሙት የምታነጹበትን ዐስቡ እንጂ ትዕቢትን አታስቡ፤ ሁሉም እንደ እምነቱ መጠን እግዚአብሔር እንደ አደለው ይኑር።
ሮሜ 12:1-3 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው። መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችሁ በሰጣችሁ እምነት መጠን ራሳችሁን በአግባቡ መዝኑ እንጂ፣ ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ እያንዳንዳችሁን እመክራለሁ።
ሮሜ 12:1-3 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ።
ሮሜ 12:1-3 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ ወንድሞቼ ሆይ! እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ፥ ሕያውና የተቀደሰ መሥዋዕት አድርጋችሁ ሁለንተናችሁን እንድታቀርቡ በመሐሪው በእግዚአብሔር ስም እለምናችኋለሁ፤ ይህም ማቅረብ የሚገባችሁ ቅንነት ያለው እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልግሎት ነው። መልካሙንና ደስ የሚያሰኘውን ፍጹም የሆነውንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ እንድትችሉ አእምሮአችሁን በማደስ ሕይወታችሁ ይለወጥ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉት። ደግሞም እያንዳንዳችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ እምነት መጠን በትሕትና አስቡ እንጂ ከሚገባችሁ በላይ ስለ ራሳችሁ በትዕቢት አታስቡ ብዬ በተሰጠኝ ጸጋ እነግራችኋለሁ።
ሮሜ 12:1-3 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ሰውነታችሁን ሕያው መሥዋዕት፥ ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አድርጋችሁ እንድታቀርቡ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም መንፈሳዊ አገልግሎታችሁ ነው። መልካም፥ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማወቅ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችሁ እንደሰጣችሁ እምነት መጠን፥ በረጋ አእምሮ አስቡ እንጂ ማሰብ ከሚገባችሁ በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ እናገራለሁና።