ሮሜ 1:1-5
ሮሜ 1:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማስተማር ተለይቶ ከተጠራ ሐዋርያ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ከሚሆን ከጳውሎስ፥ በነቢያቱ ቃልና በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ በተስፋ ያናገረው፥ ከዳዊት ዘር ሰው ሆኖ በሥጋ ስለ ተወለደ ስለ ልጁ፥ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በኀይሉና በመንፈስ ቅዱስ፥ ከሙታንም ተለይቶ በመነሣቱ ስለ አሳየ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በስሙ እንዲያምኑ አሕዛብን ልናስተምር ሐዋርያት ተብለን የተሾምንበትና ጸጋን ያገኘንበት፥
ሮሜ 1:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጳውሎስ፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ፣ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራና ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየ፤ ስለዚህ ወንጌል በነቢያቱ በኩል በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ተሰጠ። ወንጌሉም ስለ ልጁ፣ በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ሆነ፣ በቅድስና መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በኀይል ስለ ተገለጠው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በርሱ በኩል ስለ ስሙ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል ሰዎችን በእምነት አማካይነት ወደሚገኘው መታዘዝ ለመጥራት ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን።
ሮሜ 1:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ጳውሎስ በነቢያቱ አፍ በቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ለሰጠው ለእግዚአብሔር ወንጌል ተለየ። ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በእርሱም ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን፤
ሮሜ 1:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ከሆነው፥ ለሐዋርያነት ከተጠራው፥ የእግዚአብሔርንም ወንጌል ለማስተማር ከተመረጠው ከጳውሎስ የተላከ። ይህም ወንጌል እግዚአብሔር በነቢያት አማካይነት በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ የሰጠው የተስፋ ቃል ነው። ወንጌሉ የእግዚአብሔር ልጅ በሰብአዊነቱ በኩል፥ ከዳዊት ዘር መወለዱን የሚያበሥር ነው፤ እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድስናው መንፈስ ከሞት በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በታላቅ ኀይል ታወቀ። ስለ ክርስቶስ ስም አሕዛብ ሁሉ እንዲያምኑና እንዲታዘዙ ለማድረግ በእርሱ አማካይነት ለሐዋርያነት የሚያበቃንን ጸጋ ተቀብለናል።
ሮሜ 1:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የክርስቶስ ኢየሱስ ባርያ ጳውሎስ፥ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየ፥ ይህም ወንጌል እግዚአብሔር አስቀድሞ በነቢያቱ አማካኝነት በቅዱሳን መጻሕፍት የሰጠው ተስፋ ነው፤ ወንጌሉም ስለ ልጁ፥ በሥጋ ከዳዊት ዘር እንደመጣ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድስና መንፈስ ከሙታን በመነሣት በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ መገለጡ ነው፤ ስለ ስሙ በሕዝቦች ሁሉ መካከል ለእምነት መታዘዝን ለማምጣት ጸጋና ሐዋርያነትን በተቀበልንበት በእርሱ በኩል፥