ሮሜ 1:1-31
ሮሜ 1:1-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማስተማር ተለይቶ ከተጠራ ሐዋርያ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ከሚሆን ከጳውሎስ፥ በነቢያቱ ቃልና በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ በተስፋ ያናገረው፥ ከዳዊት ዘር ሰው ሆኖ በሥጋ ስለ ተወለደ ስለ ልጁ፥ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በኀይሉና በመንፈስ ቅዱስ፥ ከሙታንም ተለይቶ በመነሣቱ ስለ አሳየ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በስሙ እንዲያምኑ አሕዛብን ልናስተምር ሐዋርያት ተብለን የተሾምንበትና ጸጋን ያገኘንበት፥ እናንተም ዛሬ በኢየሱስ ክርስቶስ ለማመን እንደ ተጠራችሁ። በሮሜ ላላችሁ፥ እግዚአብሔር ለሚወዳችሁ፥ ለመረጣችሁና ላከበራችሁ ሁሉ፥ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን። አስቀድሜ ስለ ሁላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፤ ማመናችሁ በዓለም ሁሉ ተሰምታለችና። ባለማቋረጥ በምጸልየው ጸሎት እንደማስባችሁ ልጁ በአስተማረው ወንጌል በፍጹም ልቡናዬ የማመልከው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። ወደ እናንተ እመጣ ዘንድም እግዚአብሔር በፈቃዱ መንገዴን ያቃናልኝ ዘንድ ዘወትር እጸልያለሁ። ትጸኑ ዘንድ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እንድታገኙ ላያችሁ እወዳለሁና፤ ይህንም ማለቴ በመካከላችን ባለች በእናንተና በእኔ እምነት አብረን በእናንተ እንድንጽናና ነው። ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ፥ በሌሎች አሕዛብ እንደ ሆነ በእናንተም ዋጋዬን አገኝ ዘንድ ሁልጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ እንደ ወደድሁ፥ እስከ ዛሬ ድረስም እንደ ተሳነኝ ልታውቁ እወድዳለሁ። ለአረማውያንና ላልተማሩ፥ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም ሁሉ አስተምር ዘንድ ዕዳ አለብኝ። ይልቁንም በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ወንጌልን ላስተምራችሁ እተጋለሁ። ወንጌልን ለማስተማር አላፍርምና፤ አስቀድሞ አይሁዳዊን፥ ደግሞም አረማዊን፥ የሚያምኑበትን ሁሉ የሚያድናቸው የእግዚአብሔር ኀይሉ ነውና። “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ብሎ መጽሐፍ እንደ ተናገረ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና። እውነትን ዐውቀው በክፋታቸው በሚለውጡአት በዐመፀናውና በኀጢአተናው ሰው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ከሰማይ ይመጣል። እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው እግዚአብሔርን ማወቅ በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና። የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኀይሉና ጌትነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ የፈጠረውን ፍጥረት በማሰብና በመመርመር ይታወቃል፤ መልስ የሚሰጡበትን ምክንያት እንዳያገኙ። እግዚአብሔርን ሲያውቁት እንደ እግዚአብሔርነቱ አላከበሩትም፤ አላመሰገኑትምም፤ ነገር ግን ካዱት፤ በአሳባቸውም ረከሱ፤ ልቡናቸውም ባለማወቅ ጨለመ። ጥበበኞች ነን ሲሉ አላዋቆች ሆኑ። የማይሞተውን የእግዚአብሔርን ክብር በሚሞት ሰውና በዎፎች፥ አራት እግር ባላቸውም፥ በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ። ስለዚህም እግዚአብሔር እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵሰት አሳልፎ ተዋቸው። የእግዚአብሔርን እውነት ሐሰት አድርገዋታልና፤ ተዋርደውም ፍጥረቱን አምልከዋልና፤ ሁሉን የፈጠረውን ግን ተዉት፤ እርሱም ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ ነው፤ አሜን። ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ መቅሠፍትን አመጣባቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ትተው ለባሕርያቸው የማይገባውን ሠሩ። ወንዶችም እንዲሁ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን ትተው በፍትወት ተቃጠሉ፤ እርስ በርሳቸውም እየተመላለሱ፥ ወንዶች በወንዶች ላይ የሚያዋርዳቸውን ነውር ሠሩ፤ ነገር ግን ፍዳቸውን ያገናሉ፤ ፍዳቸውም በራሳቸው ይመለሳል። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱ መጠን እንዲሁ እግዚአብሔር ይህን የማይገባውን ይሠሩ ዘንድ ሰነፍ አእምሮን ሰጣቸው። እነርሱም ዐመፅን ሁሉ፥ ክፋትንም፥ ምኞትንም፥ ቅሚያንም፥ ቅናትንም የተመሉ ናቸው፤ ምቀኞች፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ ከዳተኞች፥ ተንኰለኞች፥ ኩሩዎች፥ ጠባያቸውንና ግብራቸውንም ያከፉ ናቸው። ሐሜተኞች፥ እግዚአብሔርን የሚጠሉ፥ ተሳዳቢዎች፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክሕተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸውም የማይታዘዙ ናቸው። የማያስተውሉ፥ ዝንጉዎች፥ ፍቅርም፥ ምሕረትም የሌላቸው ናቸው።
ሮሜ 1:1-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጳውሎስ፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ፣ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራና ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየ፤ ስለዚህ ወንጌል በነቢያቱ በኩል በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ተሰጠ። ወንጌሉም ስለ ልጁ፣ በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ሆነ፣ በቅድስና መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በኀይል ስለ ተገለጠው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በርሱ በኩል ስለ ስሙ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል ሰዎችን በእምነት አማካይነት ወደሚገኘው መታዘዝ ለመጥራት ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን። እናንተም ራሳችሁ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሆኑ ከተጠሩት መካከል ናችሁ። በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱሳን ለመሆን ለተጠራችሁ በሮም ላላችሁ ሁሉ፤ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ከሁሉ አስቀድሜ፣ እምነታችሁ በዓለም ሁሉ በመሰማቱ፣ ስለ ሁላችሁ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ። ሁልጊዜ ምን ያህል እንደማስባችሁ፣ የልጁን ወንጌል በመስበክ በሙሉ ልቤ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፤ በጸሎቴ ሁልጊዜ አስባችኋለሁ፤ አሁን ደግሞ በመጨረሻ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ እናንተ እንድመጣ መንገድ ይከፈትልኝ ዘንድ እጸልያለሁ። እንድትጸኑ የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ አካፍላችሁ ዘንድ፣ ላያችሁ እናፍቃለሁ። ይኸውም እናንተና እኔ በእያንዳንዳችን እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው። ወንድሞች ሆይ፤ በሌሎች አሕዛብ ዘንድ እንደ ሆነልኝ፣ በእናንተም ዘንድ ፍሬ ለማግኘት ብዙ ጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ ዐቅጄ ሳለሁ፣ እስከ አሁን ድረስ ግን መከልከሌን እንድታውቁ እወድዳለሁ። ግሪኮች ለሆኑትና ላልሆኑት፣ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉ ዕዳ አለብኝ፤ በሮም ለምትኖሩ፣ ለእናንተም ወንጌልን ለመስበክ የምጓጓው ለዚህ ነው። በወንጌል አላፍርም፤ ምክንያቱም ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤ ይህም በመጀመሪያ ለአይሁድ፣ ቀጥሎም ለአሕዛብ ነው። በወንጌል የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጧልና፤ ጽድቁም ከእምነት ወደ እምነት የሆነ ነው፤ “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ተብሎ እንደ ተጻፈው። በክፋታቸው እውነትን ዐፍነው በሚይዙ፣ በዐመፃቸውና በክፋታቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል፤ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው ለእነርሱ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለእነርሱ ግልጽ አድርጎታል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ፣ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል፤ ስለዚህ ሰዎች ማመካኛ የላቸውም። እግዚአብሔርን ቢያውቁም እንኳ፣ እንደ አምላክነቱ አላከበሩትም፤ ምስጋናም አላቀረቡለትም፤ ነገር ግን ሐሳባቸው ፍሬ ቢስ ሆነ፤ የማያስተውል ልባቸው ጨለመ። ጥበበኞች ነን ቢሉም፣ ሞኞች ሆኑ፤ የዘላለም አምላክን ክብር ምዉት በሆነው ሰው፣ በወፎች፣ በእንስሳትና በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረታት መልክ መስለው ለወጡ። ስለዚህም እግዚአብሔር በኀጢአት በተሞላው የልባቸው ምኞት እርስ በርሳቸው የገዛ አካላቸውን እንዲያስነውሩ ቅድስና ለሌለው ሩካቤ ሥጋ አሳልፎ ሰጣቸው። የእግዚአብሔርን እውነት በሐሰት ለወጡ፤ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡር አመለኩ፤ አገለገሉም፤ ፈጣሪም ለዘላለም የተመሰገነ ነው። አሜን። በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር አሳፋሪ ለሆነ ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም እንኳ ለባሕርያቸው የሚገባውን ግንኙነት ባሕርያቸው ላልሆነው ግንኙነት ለወጡ። እንደዚሁም ወንዶች ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወት ተቃጠሉ፤ ወንዶች ከወንዶች ጋራ ነውር ፈጸሙ፤ በዚህም ጥፋታቸው በገዛ ራሳቸው የሚገባቸውን ቅጣት ተቀበሉ። ከዚህም በላይ በሐሳባቸው እግዚአብሔርን ማወቅ አይጠቅምም በማለታቸው፣ መደረግ የማይገባውን እንዲያደርጉ እግዚአብሔር ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው። በሁሉም ዐይነት ዐመፃ፣ ክፋት፣ ስግብግብነትና ምግባረ ብልሹነት ተሞልተዋል፤ ቅናትን፣ ነፍስ ገዳይነትን፣ ጥልን፣ አታላይነትንና ተንኰልን የተሞሉ ናቸው፤ ሐሜተኞች፣ ስም አጥፊዎች፣ አምላክን የሚጠሉ፣ ተሳዳቢዎች፣ ትዕቢተኞችና ትምክሕተኞች ናቸው፤ ክፋትን የሚሠሩበትን መንገድ ያውጠነጥናሉ፤ ለወላጆቻቸው አይታዘዙም። የማያስተውሉ፣ ውል የሚያፈርሱ፣ ርኅራኄ የሌላቸውና ጨካኞች ናቸው።
ሮሜ 1:1-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ጳውሎስ በነቢያቱ አፍ በቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ለሰጠው ለእግዚአብሔር ወንጌል ተለየ። ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በእርሱም ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን፤ በእነርሱም መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ ልትሆኑ የተጠራችሁ እናንተ ደግሞ ናችሁ። በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ በሮሜ ላላችሁት ሁሉ፥ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። እምነታችሁ በዓለም ሁሉ ስለ ተሰማች አስቀድሜ ስለ ሁላችሁ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ። በልጁ ወንጌል በመንፈሴ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና፤ ምናልባት ብዙ ቆይቼ ወደ እናንተ አሁን እንድመጣ በእግዚአብሔር ፈቃድ መንገዴን እንዲያቀናልኝ እየለመንሁ ሁልጊዜ ስጸልይ ስለ እናንተ ሳላቋርጥ አሳስባለሁ። ትጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁና፤ ይህንም ማለቴ በመካከላችን ባለች በእናንተና በእኔ እምነት አብረን በእናንተ እንድንጽናና ነው። ወንድሞች ሆይ፥ በሌሎቹ አሕዛብ ደግሞ እንደ ሆነ በእናንተም ፍሬ አገኝ ዘንድ ብዙ ጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ እንዳሰብሁ እስከ አሁን ግን እንደ ተከለከልሁ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። ለግሪክ ሰዎችና ላልተማሩም፥ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም ዕዳ አለብኝ፤ ስለዚህም በሚቻለኝ መጠን በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ልሰብክ ተዘጋጅቼአለሁ። በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና። ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና። እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣልና፤ እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና። የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ። ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፥ የማይጠፋውንም የእግዚአብሔር ክብር በሚጠፋ ሰውና በወፎች አራት እግር ባላቸውም በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ። ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን። ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ዓመፃ ሁሉ፥ ግፍ፥ መመኘት፥ ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን፥ ነፍስ መግደልን፥ ክርክርን፥ ተንኰልን፥ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፤ የሚያሾከሹኩ፥ ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚያንገላቱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት ያጡ ናቸው፤
ሮሜ 1:1-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ከሆነው፥ ለሐዋርያነት ከተጠራው፥ የእግዚአብሔርንም ወንጌል ለማስተማር ከተመረጠው ከጳውሎስ የተላከ። ይህም ወንጌል እግዚአብሔር በነቢያት አማካይነት በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ የሰጠው የተስፋ ቃል ነው። ወንጌሉ የእግዚአብሔር ልጅ በሰብአዊነቱ በኩል፥ ከዳዊት ዘር መወለዱን የሚያበሥር ነው፤ እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድስናው መንፈስ ከሞት በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በታላቅ ኀይል ታወቀ። ስለ ክርስቶስ ስም አሕዛብ ሁሉ እንዲያምኑና እንዲታዘዙ ለማድረግ በእርሱ አማካይነት ለሐዋርያነት የሚያበቃንን ጸጋ ተቀብለናል። እናንተም የኢየሱስ ክርስቶስ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ከጠራቸው ወገኖች መካከል ናችሁ። ስለዚህ በሮም ለምትኖሩ፥ እግዚአብሔር ለወደዳችሁና ወገኖቹ እንድትሆኑ ለጠራችሁ ሁሉ፦ ከአባታችን ከእግዚአብሔርና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። የእምነታችሁ ዝና በዓለም ሁሉ ስለ ተሰማ፥ ከሁሉ አስቀድሜ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ስለ ሁላችሁ አምላኬን አመሰግናለሁ። ዘወትር በጸሎቴ እንደማስባችሁ፥ ስለ ልጁ የሚናገረውን ወንጌል በማስተማር በሙሉ ልቤ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። ደግሞ አሁን በመጨረሻ ወደ እናንተ ለመምጣት የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ መንገዴ እንዲቃናልኝ ሁልጊዜ እጸልያለሁ። በእምነት እንድትጸኑ የሚያደርጋችሁን መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እመኛለሁ። ይህንንም ማለቴ እኔ በእናንተ እምነት፥ እናንተም በእኔ እምነት እርስ በእርሳችን እንድንጽናና ነው። ወንድሞቼ ሆይ! በሌሎች አሕዛብ መካከል ብዙ አማኞችን እንዳገኘሁ እንዲሁም በእናንተ መካከል አማኞችን ለማግኘት ፈልጌ ነበር፤ ነገር ግን ወደ እናንተ ለመምጣት ብዙ ጊዜ ዐቅጄ እስከ አሁን ያልተሳካልኝ መሆኑን እንድታውቁ እወዳለሁ። የሠለጠኑትንም ሆነ ያልሠለጠኑትን፥ የተማሩትንም ሆነ ያልተማሩትን ሕዝቦች የማስተማር ግዴታ አለብኝ። ስለዚህ ለእናንተም በሮም ለምትኖሩ ወንጌልን ላስተምራችሁ እመኛለሁ። እኔ በወንጌል ቃል አላፍርም፤ የወንጌል ቃል በመጀመሪያ አይሁድን፥ ቀጥሎም አሕዛብን፥ እንዲሁም የሚያምኑትን ሰዎች ሁሉ ማዳን የሚችል የእግዚአብሔር ኀይል ነው። ጻድቅ በእምነት ሕይወትን ያገኛል ተብሎ ተጽፎአል፤ የእግዚአብሔር ጽድቅም በሥራ ስለ ታየ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ሰው የሚጸድቀው በእምነት ነው። ሰዎች በክፋታቸው እውነት እንዳይታወቅ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም ባለመፍራታቸውና በክፋታቸው ምክንያት በሁሉም ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ከሰማይ ይገለጣል። የሚቀጣቸውም ስለ እግዚአብሔር ማወቅ የሚገባቸውን እግዚአብሔር ራሱ ገልጦላቸው ያውቁ ስለ ነበር ነው። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ለሰዎች የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ፥ ይኸውም ዘለዓለማዊው ኀይሉና አምላክነቱ እርሱ በፈጠራቸው ነገሮች አማካይነት ግልጥ ሆኖ ስለ ታየ ሰዎች ለሚያጠፉት ጥፋት ምክንያት የላቸውም። እነርሱ እግዚአብሔርን ዐውቀውት ሳለ ለእርሱ እንደ አምላክነቱ የሚገባውን ክብርና ምስጋና አልሰጡትም፤ በሐሳባቸውም ከንቱ ሆኑ፤ የማያስተውል ልቡናቸውም ጨለመ፤ “ጥበበኞች ነን” ሲሉ ሞኞች ሆኑ። የማያልፈውን እግዚአብሔርን በማክበር ፈንታ ኀላፊ በሆነው በሰው ምስል፥ በወፍ፥ አራት እግሮች ባሉአቸው እንስሶች፥ በመሬት ላይ በሚሳቡ እንስሶች መልክ ለተሠራው ምስል ክብርን ሰጡ። ስለዚህ እርስ በርሳቸው በገዛ አካላቸው ላይ አሳፋሪ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ እግዚአብሔር ርኲሰት ለሞላበት ለክፉ ምኞታቸው ተገዢዎች እንዲሆኑ ተዋቸው። ይህም የሆነው የእግዚአብሔርን እውነት በሐሰት ስለ ለወጡ፥ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡርን ስላመለኩና ስለ አገለገሉ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ አሜን። ሰዎች ይህን በማድረጋቸው ምክንያት እግዚአብሔር ለማይገባ አስነዋሪ ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸው እንኳ የተለመደውን ተፈጥሮአዊ ግንኙነት ባልተለመደ ግንኙነት ለወጡት። እንዲሁም ወንዶቹ የተለመደውን ግንኙነት ከሴቶች ጋር ማድረግ ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ስለዚህ ወንዶች ከወንዶች ጋር አሳፋሪ ነገር ፈጸሙ፤ በስሕተታቸውም ምክንያት የሚገባቸውን ቅጣት በሥጋቸው ይቀበላሉ። ሰዎች እግዚአብሔርን ለማወቅ ስላልፈለጉ አስነዋሪ ነገር እንዲያደርጉ እግዚአብሔር ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው። ስለዚህ በበደል፥ በክፋት፥ በሥሥት፥ በተንኰል፥ በምቀኝነት፥ በነፍሰገዳይነት፥ በጥል፥ በአታላይነት፥ በክፉ ምኞት ሁሉ የተሞሉ፥ እንዲሁም ሐሜተኞች ናቸው፤ የሰውን ስም የሚያጠፉ፥ እግዚአብሔርን የሚጠሉ፥ ሰውን የሚያዋርዱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክሕተኞች፥ ክፋትን ለማድረግ ዘዴ የሚፈልጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ጨካኞች ናቸው።
ሮሜ 1:1-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የክርስቶስ ኢየሱስ ባርያ ጳውሎስ፥ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየ፥ ይህም ወንጌል እግዚአብሔር አስቀድሞ በነቢያቱ አማካኝነት በቅዱሳን መጻሕፍት የሰጠው ተስፋ ነው፤ ወንጌሉም ስለ ልጁ፥ በሥጋ ከዳዊት ዘር እንደመጣ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድስና መንፈስ ከሙታን በመነሣት በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ መገለጡ ነው፤ ስለ ስሙ በሕዝቦች ሁሉ መካከል ለእምነት መታዘዝን ለማምጣት ጸጋና ሐዋርያነትን በተቀበልንበት በእርሱ በኩል፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ልትሆኑ በተጠራችሁ በእናንተም መካከል፥ በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁ፥ በሮሜ ላላችሁ ሁሉ፥ ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ ከአባታችን ከእግዚአብሔር ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። እምነታችሁ በዓለም ሁሉ ስለ ተሰማ፥ ስለ ሁላችሁም በመጀመሪያ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ። ያለማቋረጥ እንዴት እንደማስባችሁ የልጁን ወንጌል በመስበክ በመንፈሴ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፤ ምናልባት አሁን በመጨረሻ፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ወደ እናንተ ለመምጣት ሁልጊዜ በጸሎቴ እጠይቃለሁ። የሚያጸናችሁን መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁ፤ ይህም እርስ በእርሳችን በእናንተና በእኔ ዘንድ ባለች እምነት፥ አብረን እንድንጽናና ነው። ወንድሞች ሆይ! በሌሎቹ ሕዝቦች እንዳገኘሁት በእናንተም ፍሬ ለማግኘት ብዙ ጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ እንዳቀድሁ እስከ አሁን ግን እንደ ተከለከልሁ እንድታውቁ እወዳለሁ። ለግሪኮችና ግሪኮች ላልሆኑት፥ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉትም ዕዳ አለብኝ፤ ስለዚህ በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ልሰብክ እጓጓለሁ። በወንጌል አላፍርምና፤ በመጀመሪያ ለአይሁድ እንዲሁም ለግሪካውያን፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው። “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና። በክፋታቸው እውነትን አፍነው በሚይዙ ሰዎች፥ በዐመፃቸውና በክፋታቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ከሰማይ ይገለጣልና፤ ስለ እግዚአብሔር መታወቅ የሚገባው በእነርሱ መካከል ግልፅ ነው፤ ምክንያቱም ለእነርሱ እግዚአብሔር ግልፅ አድርጎላቸዋል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታዩት ነገሮች፥ ይኸውም ዘላለማዊው ኃይሉና መለኮታዊነቱ ታውቆ፥ ግልፅም ሆኖ ስለሚታይ ሰበብ የላቸውም። ምክንያቱም እግዚአብሔርን እያወቁት እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን አላከበሩትም ወይም አላመሰገኑትም፤ ነገር ግን ምክንያታቸው ዋጋ ቢስ ሆነ፤ የማያስተውለው ልባቸውም ጨለመ። ጥበበኞች ነን ሲሉ ሞኞች ሆኑ፤ የማይጠፋውን የእግዚአብሔርን ክብር በሚጠፋው በሰው፥ በወፎች፥ አራት እግር ባላቸው እንስሳትና በመሬት ላይ በሚሳቡ እንስሳት መልክ ምስል ለወጡ። ስለዚህ እግዚአብሔር እርስ በእርሳቸው ሥጋቸውን እንዲያዋርዱ፥ በልባቸው ፍትወት ለርኩሰት አሳልፎ ሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ለወጡ፤ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡርን አመለኩ አገለገሉትም፤ እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም የተባረከ ነው፤ አሜን። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ለሚያዋርድ ፍትወት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ተፈጥሮአዊውን ግንኙነት ተፈጥሮአዊ ባልሆነ ግንኙነት ለወጡ፤ እንዲሁም ደግሞ ወንዶች ተፈጥሮአዊ የሆነውን ከሴት ጋር መገናኘት ትተው እርስ በእርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም ከወንዶች ጋር ነውር ፈጸሙ፤ በስሕተታቸውም ምክንያት የሚገባቸውን ቅጣት በራሳቸው ላይ ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ስላልፈለጉ እግዚአብሔር ተገቢ ያልሆነውን ነገር እንዲያደርጉ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዐመፃ፥ በግፍ፥ በስስት፥ በክፋት፥ በቅናት፥ ነፍስ በመግደል፥ በጥል፥ በአታላይነት፥ በተንኮል የተሞሉ፥ የሚያሾከሹኩ፥ ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚዳፈሩ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚያውጠነጥኑ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ የማይታመኑ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት የሌላቸው ናቸው፤