ራእይ 7:1-17
ራእይ 7:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ በአራቱ የምድር ማዕዘን ቆመው አራት መላእክት አየሁ፤ እነርሱም ነፋስ በምድር ቢሆን ወይም በባሕር ወይም በማንም ዛፍ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት ያዙ። የሕያው አምላክ ማኅተም ያለውም ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፤ ምድርንና ባሕርንም ሊጐዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ “የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጕዱ፤” አላቸው። የታተሙትንም ቍጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። ከይሁዳ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፤ ከሮቤል ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከጋድ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከአሴር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከንፍታሌም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከምናሴ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከስምዖን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሌዊ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከይሳኮር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዛብሎን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዮሴፍ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከብንያም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ። ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ “ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው የአምላካችንና የበጉ ነው!” አሉ። መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶቹ ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፤ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ “አሜን በረከትና ገናናነት ጥበብም ምስጋናም ክብርም ኀይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን! አሜን።” አሉ። ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ “እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ?” አለኝ። እኔም “ጌታ ሆይ! አንተ ታውቃለህ፤” አልሁት። አለኝም “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ። ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፤ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል። ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፤ ፀሐይም ትኵሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም፤ በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፤ ወደ ሕይወትም ውሃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።”
ራእይ 7:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ አራት መላእክት በአራቱ የምድር ማእዘኖች ቆመው አየሁ፤ እነርሱም ነፋስ በምድር ወይም በባሕር፣ ወይም በማንኛውም ዛፍ ላይ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሶች ያዙ። ከዚያም የሕያው አምላክ ማኅተም ያለው ሌላ መልአክ ከምሥራቅ ሲመጣ አየሁ፤ እርሱም ምድርንና ባሕርን ለመጕዳት ሥልጣን የተሰጣቸውን አራቱን መላእክት በታላቅ ድምፅ እንዲህ አላቸው፤ “በአምላካችን ባሮች ግንባር ላይ ማኅተም እስከምናደርግባቸው ድረስ ምድርን ወይም ባሕርን፣ ወይም ዛፎችን አትጕዱ።” የታተሙትንም ቍጥር ሰማሁ፤ እነርሱም ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መቶ አርባ አራት ሺሕ ነበሩ፦ ከይሁዳ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ ታተሙ፤ ከሮቤል ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣ ከጋድ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣ ከአሴር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣ ከንፍታሌም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣ ከምናሴ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣ ከስምዖን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣ ከሌዊ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣ ከይሳኮር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣ ከዛብሎን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣ ከዮሴፍ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣ ከብንያም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ ታተሙ። ከዚህም በኋላ አየሁ፤ እነሆ፤ በዙፋኑና በበጉ ፊት ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ ቆመው ነበር፤ እነርሱም ነጭ ልብስ ለብሰው፣ የዘንባባ ዝንጣፊ በእጃቸው ይዘው ነበር። በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብለው ጮኹ፤ “ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው፣ የአምላካችንና የበጉ ነው።” መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ፣ በአራቱም ሕያዋን ፍጡራን ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑ ፊት በግንባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ እንዲህም ይሉ ነበር፤ “አሜን፤ ውዳሴና ክብር፣ ጥበብ፣ ምስጋናና፣ ሞገስ፣ ኀይልና ብርታትም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን። አሜን።” ከዚያም ከሽማግሌዎቹ አንዱ፣ “እነዚህ ነጭ ልብስ የለበሱት እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ?” አለኝ። እኔም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ታውቃለህ” አልሁት። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም ዐጥበው አንጽተዋል። ስለዚህ፣ “በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሆነው፣ ቀንና ሌሊት በመቅደሱ ያገለግሉታል፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ድንኳኑን በላያቸው ይዘረጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፤ ከዚህም በኋላ አይጠሙም፤ ፀሓይ አይመታቸውም፤ ሐሩሩም ሁሉ አያቃጥላቸውም፤ ምክንያቱም በዙፋኑ መካከል ያለው በግ እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭም ይመራቸዋል፤ እግዚአብሔር እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።”
ራእይ 7:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚህም በኋላ በአራቱ በምድር ማዕዘን ቆመው አራት መላእክት አየሁ፥ እነርሱም ነፋስ በምድር ቢሆን ወይም በባሕር ወይም በማንም ዛፍ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት ያዙ። የሕያው አምላክ ማኅተም ያለውም ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፥ ምድርንና ባሕርንም ሊጐዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ፦ የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጕዱ አላቸው። የታተሙትንም ቍጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። ከይሁዳ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፥ ከሮቤል ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከጋድ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከአሴር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከንፍታሌም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከምናሴ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከስምዖን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሌዊ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከይሳኮር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዛብሎን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዮሴፍ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከብንያም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ። ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ፦ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ። መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶቹ ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፥ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ፦ አሜን፥ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን አሉ። ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ፦ እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ። እኔም፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁት። አለኝም፦ እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ። ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፥ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፥ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል። ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፥ ፀሐይም ትኵሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም፤ በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፥ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።
ራእይ 7:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ አራት መላእክት በአራቱ የምድር ማእዘኖች ቆመው አየሁ፤ እነርሱ በምድርም ሆነ በባሕር ወይም በዛፍ ላይ ምንም ነፋስ እንዳይነፍስ ከአራቱ አቅጣጫ የሚመጡትን የምድር ነፋሶች ያዙ። የሕያው አምላክን ማኅተም የያዘ ሌላ መልአክም ከምሥራቅ ሲመጣ አየሁ፤ ምድርንና ባሕርን እንዲጐዱ ሥልጣን ወደ ተሰጣቸው ወደ አራቱ መላእክት ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “በአምላካችን አገልጋዮች ግንባር ላይ ማኅተም እስክናትምባቸው ድረስ፥ ምድርንም ሆነ ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጒዱ” ብሎ ጮኸ። የታተሙትንም ሰዎች ቊጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ የታተሙት ሰዎች ቊጥር መቶ አርባ አራት ሺህ ነበር። ከይሁዳ ነገድ የታተሙት ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሮቤል ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከጋድ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከአሴር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከንፍታሌም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከምናሴ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከስምዖን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሌዊ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከይሳኮር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዛብሎን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዮሴፍ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከብንያም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ነበሩ። ከዚህ በኋላ ተመለከትኩ፤ እጅግ ብዙ ሰዎችን አየሁ፤ እነርሱ ከሕዝብና ከነገድ፥ ከወገንና ልዩ ልዩ ቋንቋ ከሚናገሩ ሁሉ የተውጣጡ ነበሩ፤ እነዚህ ነጭ ልብስ ለብሰው፥ የዘንባባ ዝንጣፊ በእጃቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው ነበር፤ በታላቅ ድምፅ እየጮኹም፥ “ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው የአምላካችንና የበጉ ነው!” ይሉ ነበር። መላእክቱ ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶች ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑ ፊት በግንባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ እንዲህም አሉ፦ “አሜን! ውዳሴ፥ ገናናነት፥ ጥበብ፥ ምስጋና፥ ክብር፥ ኀይል፥ ብርታት ለአምላካችን ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን! አሜን።” ከሽማግሌዎቹ አንዱ ወደ እኔ መለስ ብሎ “እነዚህ ነጭ ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ?” አለኝ። እኔም “ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ” አልኩት። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “እነዚህ ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሆነው ሌሊትና ቀን በመቅደሱ ያገለግሉታል፤ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም መጠለያቸው ይሆናል። ከእንግዲህ ወዲህ አይርባቸውም፤ አይጠማቸውም፤ ፀሐይ አይመታቸውም፤ ሙቀት አያገኛቸውም፤ በዙፋኑ መካከል ያለው በግ እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭም ይመራቸዋል፤ እግዚአብሔር እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ይጠርግላቸዋል።”
ራእይ 7:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚህም በኋላ በአራቱ የምድር ማዕዘን የቆሙ አራት መላእክት አየሁ፤ እነርሱም ነፋስ በምድር ላይም ቢሆን ወይም በባሕር ላይ ወይም በማንኛውም ዛፍ ላይ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት ያዙ። የሕያው አምላክ ማኅተም ያለውም ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፤ ምድርንና ባሕርንም ሊጐዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ “የአምላካችንን ባርያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርንም ሆነ ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጉዱ፤” አላቸው። የታተሙትንም ቍጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። ከይሁዳ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፤ ከሮቤል ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከጋድ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከአሴር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከንፍታሌም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከምናሴ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከስምዖን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሌዊ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከይሳኮር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዛብሎን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዮሴፍ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከብንያም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ። ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም ማንም ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሰዎች ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ “ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው የአምላካችንና የበጉ ነው!” አሉ። መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም ሕያዋን ፍጡራን ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፤ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ “አሜን ውዳሴ፥ ክብር፥ ጥበብ፥ ምስጋና ገናናነት፥ ክብር ኃይልና ብርታት ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን! አሜን።” አሉ። ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ “እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከየትስ መጡ?” አለኝ። እኔም “ጌታ ሆይ! አንተ ታውቃለህ፤” አልሁት። እንዲህም አለኝም፦ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሶቻቸውንም አጥበው በበጉ ደም አንጽተዋል። ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ይቆማሉ፤ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ውስጥ ያመልኩታል፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ድንኳኑን በእነርሱ ላይ ይዘረጋል። ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፤ ፀሐይም ሆነ ትኩሳትም ሁሉ ከቶ አይመታቸውም፤ በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፤ ወደ ሕይወትም ውሃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።”