ራእይ 6:1-17
ራእይ 6:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በጉም ከሰባቱ ማኅተም አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፤ ከአራቱም እንስሶች አንዱ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ “መጥተህ እይ” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም አምባላይ ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤ ድልም እየነሣ ወጣ፤ ድል ለመንሣት። ሁለተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ “መጥተህ እይ” ሲል ሰማሁ። ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፤ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው። ሦስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ “መጥተህ እይ” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም ጥቁር ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ። በአራቱም እንስሶች መካከል ድምፅ “አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፥ ዘይትንና ወይንንም አትጕዳ” ሲል ሰማሁ። አራተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምፅ “መጥተህ እይ” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም ሐመር ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው። አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ “ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ! እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?” አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው። ስድስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ አየሁ፤ ታላቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ፀሐይም እንደ ማቅ ጠጕር ጥቁር ሆነ፤ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነ፤ በለስም በብርቱ ነፋስ ተናውጣ ቃርያዋን ፍሬ እንደምትጥል የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ወደቁ፤ ሰማይም እንደ መጽሐፍ ተጠቅልሎ አለፈ፤ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወሰዱ። የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኀይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዐለቶች ተሰወሩ፤ ተራራዎችንና ዐለቶችንም “በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፤ ማንስ ሊቆም ይችላል?” አሉአቸው።
ራእይ 6:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በጉም ከሰባቱ ማኅተሞች የመጀመሪያውን ሲፈታ አየሁ፤ ከዚያም ከአራቱ ሕያዋን ፍጡራን አንዱ፣ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ ነጭ ፈረስ ቆሞ ነበር፤ ተቀምጦበት የነበረውም ቀስት ይዞ ነበር፤ አክሊልም ተሰጠው፤ እርሱም እንደ ድል አድራጊ ድል ለመንሣት ወጣ። በጉ ሁለተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ሁለተኛው ሕያው ፍጡር፣ “ና!” ሲል ሰማሁ። ሌላ ፍም የሚመስል ቀይ ፈረስም ወጣ፤ ተቀምጦበት የነበረው ሰላምን ከምድር ላይ እንዲወስድና ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ለማድረግ ሥልጣን ተሰጠው፤ ትልቅም ሰይፍ ተሰጠው። በጉ ሦስተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ሦስተኛው ሕያው ፍጡር፣ “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ ጥቍር ፈረስ ቆሞ አየሁ፤ ተቀምጦበት የነበረውም በእጁ ሚዛን ይዞ ነበር። ከዚያም ከአራቱ ሕያዋን ፍጡራን መካከል፣ “አንድ እርቦ ስንዴ ለአንድ ቀን ደመወዝ፤ ሦስት እርቦ ገብስም ለአንድ ቀን ደመወዝ ይሁን፤ ዘይቱንና የወይን ጠጁን አትጕዳ” የሚል ድምፅ ሰማሁ። በጉ አራተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ አራተኛው ሕያው ፍጡር፣ “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ ግራጫ ፈረስ ቆሞ አየሁ፤ ተቀምጦበት የነበረውም ስሙ ሞት ነበር፤ ሲኦልም ከኋላ ይከተለው ነበር። እነርሱም በሰይፍ፣ በራብ፣ በመቅሠፍትና በምድር አራዊት እንዲገድሉ በምድር አንድ አራተኛ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው። ዐምስተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁትም ምስክርነት የታረዱትን ሰዎች ነፍሶች ከመሠዊያው በታች አየሁ። እነርሱም በታላቅ ድምፅ፣ “ሁሉን የምትገዛ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ አትፈርድም? እስከ መቼስ ደማችንን በምድር በሚኖሩት ላይ አትበቀልም?” አሉ። ከዚያም ለእያንዳንዳቸው ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤ ወደ ፊት እንደ እነርሱ የሚገደሉ የአገልጋይ ባልንጀሮቻቸውና ወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪሞላ ድረስ ጥቂት ጊዜ እንዲታገሡ ተነገራቸው። ስድስተኛውን ማኅተም ሲፈታ ተመለከትሁ፤ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ፀሓይም እንደ ማቅ ጠቈረች፤ ጨረቃም በሙሉ እንደ ደም ቀላች። የበለስ ዛፍ በብርቱ ነፋስ ስትወዛወዝ ያልበሰለው ፍሬ ከርሷ እንደሚረግፍ፣ የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ረገፉ። ሰማይ እንደ ጥቅልል መጽሐፍ ተጠቅልሎ ዐለፈ፤ ተራሮችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወገዱ። ከዚህ በኋላ የምድር ነገሥታትና ገዦች፣ የጦር መኰንኖች፣ ሀብታሞች፣ ብርቱዎች፣ ባሮችና ጌቶች ሁሉ በዋሻዎችና በተራሮች ዐለት ውስጥ ተሸሸጉ፤ ተራሮቹንና ዐለቶቹንም፣ “በላያችን ውደቁ፤ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤ ታላቁ የቍጣቸው ቀን መጥቷልና፤ ማንስ ሊቆም ይችላል?” አሏቸው።
ራእይ 6:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በጉም ከሰባቱ ማኅተም አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ከአራቱም እንስሶች አንዱ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። አየሁም፥ እነሆም፥ አምባላይ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፥ አክሊልም ተሰጠው፥ ድልም እየነሣ ወጣ ድል ለመንሣት። ሁለተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፥ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው። ሦስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። አየሁም፥ እነሆም፥ ጕራቻ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ። በአራቱም እንስሶች መካከል ድምፅ፦ አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፥ ዘይትንና ወይንንም አትጕዳ ሲል ሰማሁ። አራተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምፅ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። አየሁም፥ እነሆም፥ ሐመር ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው። አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፦ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው። ስድስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ታላቅም የምድር መናወጥ ሆነ፥ ፀሐይም እንደ ማቅ ጠጕር ጥቁር ሆነ፥ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነ፥ በለስም በብርቱ ነፋስ ተናውጣ ቃርያዋን ፍሬ እንደምትጥል የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ወደቁ፥ ሰማይም እንደ መጽሐፍ ተጠቅልሎ አለፈ፥ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወሰዱ። የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ፥ ተራራዎችንና ዓለቶችንም፦ በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፥ ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው።
ራእይ 6:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህም በኋላ በጉ ከሰባቱ ማኅተሞች የመጀመሪያውን ሲከፍት አየሁ። ከአራቱ እንስሶች አንዱ እንደ ነጐድጓድ በሚያስገመግም ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ። እነሆ ነጭ ፈረስ አየሁ፤ በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ቀስት ይዞ ነበር፤ አክሊልም ተሰጠው፤ እርሱም ድል ነሺ ሆኖ ከድል ወደ ድል ለመሄድ ወጣ። በጉ ሁለተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ፥ ሁለተኛው እንስሳ “ና!” ሲል ሰማሁ። ሌላ ደማቅ ቀይ ፈረስ ወጣ፤ በፈረሱ ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር እንዲያስወግድና ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲተላለቁ ለማድረግ ሥልጣን ተሰጠው፤ ትልቅ ሰይፍም ተሰጠው። በጉ ሦስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ “ና!” ሲል ሰማሁ፤ እነሆ ጥቊር ፈረስ አየሁ፤ በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ሚዛን በእጁ ይዞ ነበር፤ ከአራቱ እንስሶች መካከል የመጣ የሚመስል ድምፅ ሰማሁ፤ ይህ ድምፅ “ግማሽ ኪሎ ያኽል ስንዴ የአንድ ቀን ደመወዝ፥ ለአንድ ኪሎ ተኩል ያኽል ገብስ ለአንድ ቀን ደመወዝ ይሁን፤ ዘይትንና ወይንን ግን አትጒዳ!” ሲል ሰማሁ። በጉ አራተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ የአራተኛውን እንስሳ ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ፤ እነሆ ግራጫ ፈረስ አየሁ፤ በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ይባል ነበር፤ ሲኦልም ይከተለው ነበር፤ ሞትና ሲኦልም የምድርን አንድ አራተኛ እጅ በጦርነት፥ በራብ፥ በቸነፈርና በምድር አራዊት እንዲገድሉ ሥልጣን ተሰጣቸው። አምስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ሰጡትም ምስክርነት የተገደሉትን ሰዎች ነፍሶች ከመሠዊያው በታች አየሁ፤ እነርሱ በታላቅ ድምፅ “ቅዱስና እውነተኛ፥ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፥ በምድር ባሉት ሰዎች ላይ የማትፈርደውና ስለ ደማችንም የማትበቀለው እስከ መቼ ነው!” እያሉ ጮኹ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤ እንደ እነርሱ ገና የሚገደሉ፥ እንደእነርሱ አገልጋዮች የሆኑ የጓደኞቻቸውና የወንድሞቻቸው ቊጥር እስኪሞላ ድረስ ጥቂት ጊዜ ዐርፈው እንዲቈዩ ተነገራቸው። ከዚህ በኋላ በጉ ስድስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለከትኩ፤ እነሆ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ፀሐይ እንደ ጥቊር የሐዘን ልብስ ጠቈረች፤ ጨረቃም በሙሉ እንደ ደም ቀላች፤ በክረምት ወራት ብርቱ ነፋስ የበለስን ዛፍ ሲያወዛውዝ ፍሬው ከዛፉ ላይ እንደሚረግፍ የሰማይ ኮከቦችም ረገፉ። ሰማይም እንደ ብራና ተጠቅሎ ተወገደ፤ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወሰዱ። የምድር ነገሥታት፥ ገዢዎች፥ የጦር አለቆች፥ ሀብታሞች፥ ኀይለኞች፥ አገልጋዮችና ጌቶችም ሁሉ በዋሻዎችና በተራራዎች አለቶች ውስጥ ተሸሸጉ፤ ተራራዎቹንና አለቶቹንም “ጋርዱን! በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ፊት፥ ከበጉም ቊጣ ሰውሩን! ታላቁ የቊጣ ቀን መጥቶአል፤ ማን ሊቋቋመው ይችላል?” አሉአቸው።
ራእይ 6:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በጉም ከሰባቱ ማኅተሞች አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፤ ከአራቱም ሕያዋን ፍጡራን አንዱ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ “ና” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም ነጭ ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤ ድል እየነሣ፥ ድልም ለመንሣት ወጣ። ሁለተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ “ና” ሲል ሰማሁ። ሌላም ደማቅ ቀይ ፈረስ ወጣ፤ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ፥ ሰላምን ከምድር ያስወግድ ዘንድ በእርሱ ላይ ለተቀመጠው ሥልጣን ተሰጠው፤ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው። ሦስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ “ና” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም ጥቁር ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ። በአራቱም ሕያዋን ፍጡራን መካከል እንደ ድምፅ ሰማሁ፦ “አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፥ ዘይትንና ወይንን ግን አትጉዳ” ሲል ሰማሁ። አራተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምፅ “ና” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም የገረጣ ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው። አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክርነት የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ “ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ! እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?” አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤ እንደ እነርሱም መገደል የሚጠብቃቸውን የሌሎች አገልጋዮች የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪሞላ ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተነገራቸው። ስድስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ አየሁ፤ ታላቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ፀሐይም እንደ ማቅ ጠጉር ጥቁር ሆነች፤ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነች፤ በለስም በብርቱ ነፋስ ስትናውጥ ያልበሰለ ፍሬ እንደሚረግፍ የሰማይ ከዋክብትም ወደ ምድር ወደቁ፤ ሰማይም እንደ መጽሐፍ ተጠቅልሎ አለፈ፤ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወገዱ። የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም፥ ሀብታሞችም፥ ኃይለኞችም፥ አገልጋዮችም፥ ጌቶችም ሁሉ በዋሻዎችና በተራራዎች ዐለቶች ውስጥ ተሰወሩ፤ ተራራዎችንና ዐለቶችንም “በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቁጣ ሰውሩን፤ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፤ ማንስ ጸንቶ ሊቆም ይችላል?” አሉአቸው።