ራእይ 5:1-6

ራእይ 5:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ቀኝ እጅ፥ በውስጥና በውጪ የተጻፈበት በሰባት ማኅተም የታሸገ የብራና ጥቅል መጽሐፍ አየሁ፤ አንድ ብርቱ መልአክ በታላቅ ድምፅ “ማኅተሞቹን መፍታትና የብራናውን ጥቅል መጽሐፍ መክፈት የሚገባው ማን ነው?” ብሎ ሲናገር አየሁ። ነገር ግን በሰማይም ሆነ በምድር ወይም ከምድር በታች የብራናውን ጥቅል መጽሐፍ መክፈትና ውስጡን መመልከት የተቻለው ማንም አልነበረም። የብራናውን ጥቅል መጽሐፍ መክፈትና ውስጡን መመልከት የሚገባው ስላልተገኘ በጣም አለቀስኩ፤ በዚያን ጊዜ ከሽማግሌዎቹ አንዱ “አታልቅስ፤ እነሆ ከይሁዳ ነገድ የሆነው ከዳዊት የትውልድ ሐረግ የተነሣ አንበሳ ድል ነሥቶአል፤ እርሱ የብራናውን ጥቅል መጽሐፍና ሰባቱን ማኅተሞች መክፈት ይችላል” አለኝ። ከዚህ በኋላ በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከል፥ በሽማግሌዎችም መካከል የታረደ የሚመስል በግ ቆሞ አየሁ፤ ይህ በግ ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዐይኖች ነበሩት፤ እነርሱ ወደ ዓለም ሁሉ የተላኩ ሰባቱ የእግዚአብሔር መንፈሶች ናቸው።