ራእይ 20:1-12

ራእይ 20:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፤ ሺህ ዓመትም አሰረው፤ ወደ ጥልቅም ጣለው፤ አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት፤ ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታ ዘንድ ይገባዋል። ዙፋኖችንም አየሁ፤ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፥ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ። የቀሩቱ ሙታን ግን ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት አልኖሩም። ይህ የፊተኛው ትንሣኤ ነው። በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ። ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤ በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፥ ጎግንና ማጎግን እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው። ወደ ምድርም ስፋት ወጡ፤ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው። ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሰቃያሉ። ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፤ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ፤ ስፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ፤ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ።

ራእይ 20:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የጥልቁን መክፈቻና ትልቅ ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። እርሱም የጥንቱን እባብ፣ ዘንዶውን፣ ማለትም ዲያብሎስን ወይም ሰይጣንን ይዞ ሺሕ ዓመት አሰረው። ሺሑ ዓመት እስኪፈጸምም ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝቦችን እንዳያስት ወደ ጥልቁ ጣለው፤ ዘጋውም፤ በርሱም ላይ ማኅተም አደረገበት። ከዚያ በኋላ ለጥቂት ጊዜ ሊፈታ ይገባዋል። ቀጥሎም ዙፋኖችን አየሁ፤ በዙፋኖቹም ላይ ለመፍረድ ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎች ተቀምጠው ነበር፤ ደግሞም ስለ ኢየሱስ ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል የተሰየፉትን ሰዎች ነፍሶች አየሁ። እነርሱ ለአውሬው ወይም ለርሱ ምስል አልሰገዱም፤ በግንባራቸው ወይም በእጃቸው ላይ የአውሬውን ምልክት አልተቀበሉም፤ እነርሱም ከሞት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋራ ሺሕ ዓመት ነገሡ። የቀሩት ሙታን ግን ሺሑ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ከሞት አልተነሡም። ይህ የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው። በመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሚሆኑ ብፁዓንና ቅዱሳን ናቸው። ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከርሱም ጋራ ሺሕ ዓመት ይነግሣሉ። ሺሑም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤ በአራቱ የምድር ማእዘናት ያሉትን ሕዝቦች፣ ጎግንና ማጎግን እያሳተ ለጦርነት ሊያሰልፋቸው ይወጣል። ቍጥራቸው በባሕር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ነው። እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ ወጥተው የቅዱሳንን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ ነገር ግን እሳት ከሰማይ ወርዶ በላቸው። ያሳታቸው ዲያብሎስም፣ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ እነርሱም ቀንና ሌሊት ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሠቃያሉ። ከዚህ በኋላ ታላቅ ነጭ ዙፋንና በርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ። ምድርና ሰማይ ከፊቱ ሸሹ፤ ስፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። ሌላም መጽሐፍ፣ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ተከፈተ፤ ሙታንም በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው መሠረት እንደ ሥራቸው መጠን ተፈረደባቸው።

ራእይ 20:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፥ ሺህ ዓመትም አሰረው፥ ወደ ጥልቅም ጣለው አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት፤ ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታ ዘንድ ይገባዋል። ዙፋኖችንም አየሁ፥ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፥ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ። የቀሩቱ ሙታን ግን ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት አልኖሩም። ይህ የፊተኛው ትንሣኤ ነው። በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ። ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፥ በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፥ ጎግንና ማጎግን፥ እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው። ወደ ምድርም ስፋት ወጡ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው። ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ። ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፥ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ ስፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ።

ራእይ 20:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ የጥልቁን ጒድጓድ መክፈቻና ትልቅ ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ዘንዶውንም ይዞ ሺህ ዓመት አሰረው፤ ይህም ዘንዶ ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን የሚባለው የቀድሞው እባብ ነው፤ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ሕዝቦችን እንዳያስት መልአኩ ዘንዶውን ወደ ጥልቁ ጒድጓድ ጣለው፤ ዘግቶም በማኅተም አሸገው፤ ከዚያ በኋላ ለጥቂት ጊዜ መፈታት ይገባዋል። ከዚህ በኋላ ዙፋኖችን አየሁ፤ በዙፋኖቹም ላይ የመፍረድ ሥልጣን የተሰጣቸው ተቀምጠው አየሁ፤ ስለ ኢየሱስ በመመስከራቸውና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሶች አየሁ፤ እነርሱ ለአውሬውና ለምስሉ ያልሰገዱ፥ ምልክቱንም በግንባራቸውም ሆነ በእጃቸው ላይ ያላደረጉ ናቸው፤ እነርሱ ከሞት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ነገሡ። የቀሩት ሙታን ግን ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ከሞት አልተነሡም፤ ይህም የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው፤ የመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሆኑ የተመሰገኑና ቅዱሳን ናቸው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ እነርሱ የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ይነግሣሉ። ሺህ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤ በዓለም ሁሉ የሚገኙትን ሕዝቦች ማለት ጎግንና ማጎግን ሊያስትና ለጦርነትም ሊያስከትት ይወጣል፤ ቊጥራቸው በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነው፤ እነርሱ ወደ ምድር ሁሉ ተሠራጭተው የቅዱሳንን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ ነገር ግን እሳት ከሰማይ ወርዶ በማቃጠል ደመሰሳቸው። ያሳታቸው ዲያብሎስ፥ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት በዲን በሚቃጠል እሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ፤ በዚያም ሌሊትና ቀን ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሠቃያሉ። ከዚህ በኋላ ታላቅ ነጭ ዙፋንና በዙፋኑም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፤ ምድርና ሰማይ ከፊቱ ሸሹ፤ ስፍራም አልተገኘላቸውም፤ ታናናሾችንና ታላላቆችን ሙታን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ የሕይወት መጽሐፍ የሆነ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ፤ ሙታንም በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው ሥራቸው መሠረት ፍርድ ተቀበሉ፤

ራእይ 20:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን፥ የቀደሞውን እባብ፥ ዘንዶውን ያዘው፤ ሺህ ዓመትም አሰረው፤ ወደ ጥልቅም ጣለው፤ አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት፤ ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ መፈታት ይገባዋል። ዙፋኖችንም አየሁ፤ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት የመፍረድ ሥልጣን ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርነትና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፥ እንዲሁም ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ እንደገና ሕያው ሆነው ከክርስቶስም ጋር ለሺህ ዓመት ነገሡ። የቀሩቱ ሙታን ግን ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ እንደገና በሕይወት አልኖሩም። ይህ የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው። የመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሆነ ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ይልቁንም የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእርሱም ጋር ለሺህ ዓመት ይነግሣሉ። ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤ በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፥ ጎግንና ማጎግን ለማሳትና ለጦርነት ለማስከተት ይወጣል፤ ቁጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ ነው። ወደ ምድርም ስፋት ወጡ፤ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ ነገር ግን እሳት ከሰማይ ወርዳ በላቻቸው። ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ ከዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ቀንና ሌሊት ይሰቃያሉ። ታላቅና ነጭ ዙፋን፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፤ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ፤ ስፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንን፥ እንዲሁም ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላም መጽሐፍ ተከፈተ፤ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት በተጻፈው መሠረት፥ እንደ ሥራቸው መጠን ፍርድን ተቀበሉ።