መዝሙር 85:1-13

መዝሙር 85:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አቤቱ፥ ጆሮ​ህን ወደ እኔ አዘ​ን​ብል ስማ​ኝም፥ ድሃና ምስ​ኪን ነኝና። እኔ የዋህ ነኝና ነፍ​ሴን ጠብ​ቃት፤ አም​ላኬ ሆይ፥ አን​ተን የታ​መ​ነ​ውን ባሪ​ያ​ህን አድ​ነው። አቤቱ፥ ቀኑን ሁሉ ወደ አንተ እጮ​ኻ​ለ​ሁና ይቅር በለኝ። የባ​ሪ​ያ​ህን ነፍስ ደስ አሰ​ኛት፥ ነፍ​ሴን ወደ አንተ አነ​ሣ​ለ​ሁና። አቤቱ፥ አንተ መሓ​ሪና ይቅር ባይ ነህና፥ ይቅ​ር​ታ​ህም ለሚ​ጠ​ሩህ ሁሉ ብዙ ነውና። አቤቱ፥ ጸሎ​ቴን አድ​ምጥ፥ የል​መ​ና​ዬ​ንም ቃል ስማ። ትሰ​ማ​ኛ​ለ​ህና በመ​ከ​ራዬ ቀን ወደ አንተ እጮ​ኻ​ለሁ። አቤቱ፥ ከአ​ማ​ል​ክት የሚ​መ​ስ​ልህ የለም፥ እንደ ሥራ​ህም ያለ የለም። የፈ​ጠ​ር​ሃ​ቸው አሕ​ዛብ ሁሉ ይምጡ፥ አቤቱ፥ በፊ​ት​ህም ይስ​ገዱ፥ ስም​ህ​ንም ያክ​ብሩ፤ አቤቱ፥ ድን​ቅን የም​ታ​ደ​ርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ አን​ተም ብቻ​ህን ታላቅ አም​ላክ ነህና፥ አቤቱ መን​ገ​ድ​ህን ምራኝ፥ በእ​ው​ነ​ት​ህም እሄ​ዳ​ለሁ፤ ስም​ህ​ንም ለመ​ፍ​ራት ልቤን ደስ ይለ​ዋል። አቤቱ፥ አም​ላኬ ሆይ፥ በልቤ ሁሉ አመ​ሰ​ግ​ን​ሃ​ለሁ። ለዘ​ለ​ዓ​ለ​ምም ስም​ህን አከ​ብ​ራ​ለሁ፤ ምሕ​ረ​ትህ በእኔ ላይ ታላቅ ናትና፥ ነፍ​ሴ​ንም ከታ​ች​ኛ​ዪቱ ሲኦል አድ​ነ​ሃ​ታ​ልና።

መዝሙር 85:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር ሆይ፤ ለምድርህ በጎ ውለሃል፤ የያዕቆብንም ምርኮ መለስህ። የሕዝብህን በደል ይቅር አልህ፤ ኀጢአታቸውንም ሁሉ ሸፈንህ። ሴላ መዓትህን ሁሉ አራቅህ፤ ከብርቱ ቍጣህም ተመለስህ። መድኀኒታችን የሆንህ አምላክ ሆይ፤ መልሰን፤ በእኛ ላይ የተቃጣውን ቍጣህን መልሰው። የምትቈጣን ለዘላለም ነውን? ቍጣህስ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይቀጥላልን? ሕዝብህ በአንተ ሐሤት ያደርግ ዘንድ፣ መልሰህ ሕያዋን አታደርገንምን? እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህን አሳየን፤ ማዳንህን ለግሰን። እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን እሰማለሁ፤ ለሕዝቡ፣ ለቅዱሳኑ ሰላምን ይናገራልና፤ ዳሩ ግን ወደ ከንቱ ምግባራቸው አይመለሱ። ክብሩ በምድራችን ይኖር ዘንድ፣ ማዳኑ ለሚፈሩት በርግጥ ቅርብ ነው። ምሕረትና ታማኝነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተቃቀፉ። ታማኝነት ከምድር በቀለች፤ ጽድቅም ከሰማይ ተመለከተች። እግዚአብሔር በጎ ነገር ይለግሳል፤ ምድራችንም ፍሬዋን ትሰጣለች። ጽድቅ በፊቱ ይሄዳል፤ ለአረማመዱም መንገድ ያዘጋጃል።

መዝሙር 85:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር ሆይ! ለምድርህ ምሕረትን አሳየህ፤ የያዕቆብን ዘር እንደገና አበለጸግህ። የሕዝብህን በደል ይቅር አልክ፤ ኃጢአታቸውንም ሁሉ ደመሰስክ። እነርሱን ከመቈጣት ታገሥህ፤ ብርቱ ቊጣህንም መለስህ። አዳኛችን እግዚአብሔር ሆይ! ከተሰደድንበት መልሰን፤ በእኛም ላይ ያለህን ቅርታ አርቅልን። በእኛ ላይ የምትቈጣው ለዘለዓለም ነውን? ቊጣህንስ ከትውልድ ወደ ትውልድ ታስተላልፋለህን? እኛ ሕዝብህ በአንተ እንደሰት ዘንድ፥ እንደገና ሕይወትን አትዘራብንምን? እግዚአብሔር ሆይ! ዘለዓለማዊ ፍቅርህን አሳየን፤ አድነንም። እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን ቃል ልስማ፤ እንደገና በስሕተት መንገድ ካልሄዱ በቀር፥ ለሕዝቡና ለታማኞቹ ሰላምን እንደሚሰጥ ተስፋ ሰጥቶአል። ክብሩ በምድራችን ይኖር ዘንድ፥ እርሱን ለሚፈሩት አዳኝነቱ ቅርብ ነው። ፍቅርና እውነት ይተቃቀፋሉ፤ ጽድቅና ሰላም ይስማማሉ። የሰው ታማኝነት ከምድር ይፈልቃል ጽድቅም ከሰማይ ወደ ታች ይመለከታል። እግዚአብሔር ያበለጽገናል፤ ምድራችንም ብዙ የመከር ፍሬ ትሰጠናለች። ፈለጉን እንከተል ዘንድ ጽድቅ በእግዚአብሔር ፊት ይሄዳል።

መዝሙር 85:1-13

መዝሙር 85:1-13 NASV