መዝሙር 8:1-9

መዝሙር 8:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አቤቱ ጌታ​ችን፥ ስምህ በም​ድር ሁሉ እጅግ ተመ​ሰ​ገነ፥ ምስ​ጋ​ናህ በሰ​ማ​ዮች ላይ ከፍ ከፍ ብሎ​አ​ልና። ከሕ​ፃ​ና​ትና ከሚ​ጠቡ ልጆች አፍ ምስ​ጋ​ናን አዘ​ጋ​ጀህ፥ ስለ ጠላት፥ ጠላ​ት​ንና ግፈ​ኛን ታጠ​ፋው ዘንድ። የጣ​ቶ​ች​ህን ሥራ ሰማ​ዮ​ችን፥ አንተ የሠ​ራ​ሃ​ቸ​ውን፥ ጨረ​ቃ​ንና ከዋ​ክ​ብ​ትን እና​ያ​ለ​ንና። ታስ​በው ዘንድ ሰው ምን​ድን ነው? ትጐ​በ​ኘ​ውም ዘንድ የሰው ልጅ ምን​ድን ነው? ከመ​ላ​እ​ክት ጥቂት አሳ​ነ​ስ​ኸው፤ በክ​ብ​ርና በም​ስ​ጋና ዘውድ ከለ​ል​ኸው። በእ​ጆ​ች​ህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾም​ኸው፤ ሁሉን ከእ​ግ​ሮቹ በታች አስ​ገ​ዛ​ህ​ለት፥ በጎ​ች​ንም በሬ​ዎ​ች​ንም ሁሉ፥ ደግ​ሞም የም​ድረ በዳ​ውን እን​ስ​ሶች፥ የሰ​ማ​ይ​ንም ወፎች፥ የባ​ሕ​ር​ንም ዓሦች፥ በባ​ሕር መን​ገድ የሚ​ሄ​ደ​ው​ንም ሁሉ። አቤቱ፥ ጌታ​ችን፥ ስምህ በም​ድር ሁሉ እጅግ ተመ​ሰ​ገነ።