መዝሙር 71:17-24
መዝሙር 71:17-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አምላክ ሆይ፤ አንተ ከልጅነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ እኔም እስከ ዛሬ ድረስ ድንቅ ሥራህን ዐውጃለሁ። አምላክ ሆይ፤ ሳረጅና ስሸብትም አትተወኝ፤ ክንድህን ለመጪው ትውልድ፣ ኀይልህን ኋላ ለሚነሣ ሕዝብ ሁሉ፣ እስከምገልጽ ድረስ። አምላክ ሆይ፤ ጽድቅህ እስከ ሰማያት ይደርሳል፤ አንተ ታላላቅ ነገሮችን አድርገሃል፤ አምላክ ሆይ፤ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? ብዙ መከራና ጭንቅ ብታሳየኝም፣ ሕይወቴን እንደ ገና ታድሳለህ፤ ከምድር ጥልቅም፣ እንደ ገና ታወጣኛለህ። ክብሬን ትጨምራለህ፤ ተመልሰህም ታጽናናኛለህ። አምላኬ ሆይ፤ ስለ ታማኝነትህ፣ በበገና አመሰግንሃለሁ፤ የእስራኤል ቅዱስ ሆይ፤ በመሰንቆ እዘምርልሃለሁ። ዝማሬ በማቀርብልህ ጊዜ ከንፈሮቼ በደስታ ይሞላሉ፤ አንተ የተቤዠሃትም ነፍሴ እልል ትላለች። አንደበቴ ስለ ጽድቅህ፣ ቀኑን ሙሉ ያወራል፤ የእኔን መጐዳት የሚፈልጉ፣ ዐፍረዋልና፤ ተዋርደዋልም።
መዝሙር 71:17-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! አንተ ከልጅነቴ ጀምረህ አስተማርከኝ፤ ገና አሁንም ድንቅ ሥራህን እናገራለሁ። አምላክ ሆይ! ሥልጣንህን ለሚመጣው ትውልድ፥ ኀይልህንም ለሚመጡት ሁሉ እስክገልጥና አርጅቼ እስክሸብት ድረስ እንኳ አትተወኝ። አምላክ ሆይ! ጽድቅህ እስከ ሰማይ ይደርሳል፤ ታላላቅ ነገሮችን አድርገሃል፤ አምላክ ሆይ! አንተን የሚመስል ማን ነው? በብዙ ችግርና መከራ እንድሠቃይ አድርገኸኛል፤ ሆኖም እንደገና ከመሬቱ ጥልቅ ጒድጓድ አውጥተህ አዲስ ሕይወትን ትሰጠኛለህ። ክብሬን ታሳድጋለህ፤ እንደገናም ታጽናናኛለህ። አምላኬ፥ የእስራኤል ቅዱስ ሆይ! ስለ ታማኝነትህ በበገና አመሰግንሃለሁ፤ በመሰንቆም የምስጋና መዝሙር አቀርብልሃለሁ። ያዳንከኝ እኔ የምስጋና መዝሙር ስዘምርልህ። ከንፈሮቼ የደስታ ጩኸት ይጮኻሉ። ሊጐዱኝ የሚፈልጉ ስላፈሩና ግራ ስለ ተጋቡ አንደበቴ ቀኑን ሙሉ ስለ እውነተኛ ርዳታህ ይናገራል።
መዝሙር 71:17-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አምላኬ፥ ከታናሽነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፥ እስከ ዛሬም ተኣምራትህን እነግራለሁ። እስካረጅም እስክሸመግልም ድረስ፥ ለሚመጣ ትውልድም ሁሉ ክንድህን ኃይልህንም ጽድቅህንም እስክነግር ድረስ፥ አቤቱ፥ አትተወኝ። አቤቱ፥ ጽድቅህ እስከ አርያም ይደርሳል፥ ታላላቅ ነገሮችን አድርገሃል፥ አምላክ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? ብዙ ጭንቀትንና መከራን አሳይተኸኛልና፥ ተመለስህ ሕያውም አደረግኸኝ፥ ከምድር ጥልቅም እንደገና አወጣኸኝ። ክብሬን ታበዛለህ፥ ተመልሰህም ደስ ታሰኘኛለህ፥ እኔም በበገና ስለ እውነትህ አመሰግንሃለሁ፥ የእስራኤል ቅዱስ አምላክ ሆይ፥ በመሰንቆ እዘምርልሃለሁ። ዝማሬን ባቀርብሁልህ ጊዜ ከንፈሮቼ ደስ ይላቸዋል፥ አንተ ያዳንሃትም ነፍሴ እንዲሁ። ጉዳቴን የሚሹ ባፈሩና በተነወሩ ጊዜ አንደበቴ ደግሞ ሁልጊዜ ጽድቅህን ይናገራል።