መዝሙር 7:1-17

መዝሙር 7:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አቤቱ፥ አም​ላኬ፥ በአ​ንተ ታመ​ንሁ፥ አት​ጣ​ለ​ኝም፤ ከሚ​ከ​ብ​ቡኝ ሁሉ አድ​ነ​ኝና አው​ጣኝ፥ ነፍ​ሴን እንደ አን​በሳ እን​ዳ​ይ​ነ​ጥ​ቋት፥ የሚ​ያ​ድ​ንና የሚ​ታ​ደግ ሳይ​ኖር። አቤቱ አም​ላኬ፥ እን​ዲ​ህስ ካደ​ረ​ግሁ፥ ዐመ​ፃም በእጄ ቢኖር፥ ክፉ ላደ​ረ​ጉ​ብ​ኝም ክፉን መል​ሼ​ላ​ቸው ብሆን፥ ጠላ​ቶቼ ዕራ​ቁ​ቴን ይጣ​ሉኝ። ጠላት ነፍ​ሴን ያሳ​ድ​ዳት፤ ያግ​ኛ​ትም፥ ሕይ​ወ​ቴን በም​ድር ላይ ይር​ገ​ጣት፤ ክብ​ሬ​ንም በት​ቢያ ላይ ያዋ​ር​ደው። አቤቱ፥ በመ​ዓ​ትህ ተነሥ፤ በጠ​ላ​ቶቼ ላይ ተነ​ሣ​ባ​ቸው፤ አቤቱ፥ አም​ላኬ፥ ባዘ​ዝ​ኸው ሥር​ዐት ተነሥ። የአ​ሕ​ዛ​ብም ጉባኤ ይከ​ብ​ብ​ሃል፤ ስለ​ዚ​ህም ወደ አር​ያም ተመ​ለስ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በሕ​ዝብ ላይ ይፈ​ር​ዳል፤ አቤቱ አም​ላኬ፥ እንደ ጽድ​ቅህ ፍረ​ድ​ልኝ፤ እንደ የዋ​ህ​ነ​ቴም ይሁ​ን​ልኝ። የኃ​ጥ​ኣን ክፋት ያል​ቃል፥ ጻድ​ቃ​ንን ግን ታቃ​ና​ቸ​ዋ​ለህ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልቡ​ና​ንና ኵላ​ሊ​ትን ይመ​ረ​ም​ራል። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በእ​ው​ነት ይረ​ዳ​ኛል ልበ ቅኖ​ችን የሚ​ያ​ድ​ና​ቸው እርሱ ነው። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የእ​ው​ነት ዳኛ ነው፤ ኀይ​ለ​ኛም ታጋ​ሽም ነው፤ ሁል​ጊ​ዜም ጥፋ​ትን አያ​መ​ጣም። ባት​መ​ለሱ ግን ሰይ​ፉን ይመ​ዝ​ዛል፥ ቀስ​ቱን ገተረ አዘ​ጋ​ጀም፤ የሚ​ገ​ድል መር​ዝ​ንም አዘ​ጋ​ጀ​በት፤ ፍላ​ጻ​ዎ​ቹ​ንም የሚ​ቃ​ጠሉ አደ​ረገ። እነሆ፥ ዐመ​ፀኛ በዐ​መፁ ተጨ​ነቀ፤ ጭን​ቅን ፀነሰ፤ ኀጢ​አ​ት​ንም ወለደ። ጕድ​ጓ​ድ​ንም ማሰ፥ ቈፈ​ረም። ባደ​ረ​ገ​ውም ጕድ​ጓድ ይወ​ድ​ቃል። ጉዳቱ በራሱ ይመ​ለ​ሳል፥ ዐመ​ፃ​ውም በአ​ናቱ ላይ ትወ​ር​ዳ​ለች። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን እንደ ጽድቁ መጠን አመ​ሰ​ግ​ና​ለሁ፥ ለል​ዑል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ስም እዘ​ም​ራ​ለሁ።

መዝሙር 7:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፤ ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝ፤ ታደገኝም፤ አለዚያ እንደ አንበሳ ይዘነጣጥሉኛል፤ የሚያድነኝ በሌለበትም ይቦጫጭቁኛል። እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ይህን አድርጌ ከሆነ፣ በደልም በእጄ ከተገኘ፣ በጎ ለዋለልኝ ክፉ መልሼ ብሆን፣ ጠላቴንም በከንቱ ዘርፌ ከሆነ፣ ጠላቴ አሳድዶ ይያዘኝ፤ ሕይወቴን ከምድር ይቀላቅል፤ ክብሬንም ከዐፈር ይደባልቅ። ሴላ እግዚአብሔር ሆይ፤ በመዓትህ ተነሥ፤ በቍጣ በተነሡብኝ ላይ ተነሥ፤ አምላኬ ሆይ፤ ንቃ፤ ትእዛዝም አስተላልፍ! የሕዝቦች ጉባኤ ይክበብህ፤ አንተም ከላይ ሆነህ ግዛቸው፤ እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ ይፈርዳል። እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ጽድቄ ፍረድልኝ፤ ልዑል ሆይ፤ እንደ ቅን አካሄዴ መልስልኝ። ልብንና ኵላሊትን የምትመረምር፣ ጻድቅ አምላክ ሆይ፤ የክፉዎችን ዐመፅ አጥፋ፤ ጻድቁን ግን አጽና። ጋሻዬ ልዑል አምላክ ነው፤ እርሱ ልበ ቅኖችን ያድናቸዋል። እግዚአብሔር ጻድቅ ዳኛ ነው፤ ቍጣውንም በየዕለቱ የሚገልጥ አምላክ ነው። ሰው በንስሓ የማይመለስ ከሆነ ግን፣ ሰይፉን ይስላል፤ ቀስቱን ይገትራል። የሚገድሉ ጦር ዕቃዎቹን አሰናድቷል፤ የሚንበለበሉትን ፍላጻዎቹንም አዘጋጅቷል። ክፋትን እያማጠ ያለ ሰው፣ ቅጥፈትን አርግዞ፣ ሐሰትን ይወልዳል። ጕድጓድ ምሶ ዐፈሩን የሚያወጣ፣ በአዘጋጀው ጕድጓድ ራሱ ይገባበታል። ተንኰሉ ወደ ራሱ ይመለሳል፤ ዐመፃውም በገዛ ዐናቱ ላይ ይወርዳል። ስለ ጽድቁ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀርባለሁ፤ የልዑል እግዚአብሔርን ስም በመዝሙር አወድሳለሁ።

መዝሙር 7:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! የምተማመንብህ መማጸኛዬ አንተ ነህ፤ ከሚያሳድዱኝ ሁሉ ታደገኝ፤ አድነኝም። ካላዳንከኝ ግን እንደ አንበሳ ነጥቀው ማንም ሊታደገኝ ወደማይችል ስፍራ ይወስዱኛል፤ ሰባብረውም ያደቁኛል። እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! አንድን ሰው እንኳ በድዬ ከሆነ፥ ለወዳጄ በመልካም ፈንታ ክፉ መልሼ ከሆነ፥ ጠላቴን ያለ ምክንያት እንዲሁ ጐድቼው ከሆነ፥ ከነዚህ ሁሉ ነገሮች አንዱን እንኳ አድርጌ ከሆነ፥ ጠላቴ አሳዶ ይያዘኝ! እስከ ሞት ድረስ ይርገጠኝ በአቧራም ላይ ጥሎ ክብር ያሳጣኝ! እግዚአብሔር ሆይ! በቊጣህ ተነሥ፤ የጠላቶቼንም ቊጣ አስወግድ፤ ፍርድ እንዲስተካከል ባዘዝከው መሠረት እኔን ለመርዳት ተነሥ፤ ሕዝቦችን ሁሉ በዙሪያህ ሰብስብ፤ ከላይም ሆነህ ንገሥ። እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ ይፈርዳል፤ ጌታ ሆይ! እንደ እውነተኛነቴና እንደ ታማኝነቴ ፍረድልኝ። ኅሊናንና ልብን የምትመረምር ጻድቅ አምላክ ሆይ! የክፉዎችን ዐመፅ አጥፋ፤ የጻድቃንንም ደኅንነት ጠብቅ። ልባቸው ቅን የሆኑትን የሚያድን፥ ልዑል እግዚአብሔር፥ እርሱ ጋሻዬ ነው። እግዚአብሔር ሁልጊዜ በክፉዎች ላይ የሚፈርድ ትክክለኛ ዳኛ ነው። ክፉዎች ከክፋታቸው የማይመለሱ ከሆነም፥ እግዚአብሔር ሰይፉን ይስላል፤ ቀስቱንም ያመቻቻል። የሚገድሉ የጦር መሣሪያዎችን ያበጃል፤ እንደ እሳት የሚንበለበሉ ፍላጻዎችንም ያዘጋጃል። ኃጢአተኞች በደልን ይፀንሳሉ፤ ተንኰልን ያረግዛሉ፤ ውሸትን ይወልዳሉ። ለሌሎች ወጥመድ የሚሆን ጥልቅ ጒድጓድ ይቈፍራሉ፤ ነገር ግን በቈፈሩት ጒድጓድ ውስጥ እነርሱ ራሳቸው ይገቡበታል። የሚያመጡት ችግር በራሳቸው ላይ ይደርሳል፤ በክፉ ድርጊታቸውም ዐናታቸው ይፈጠፈጣል። ስለ እውነተኛነቱ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ ለልዑል አምላክ ስም የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ።

መዝሙር 7:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አቤቱ አምላኬ፥ በአንተ ታመንሁ፥ ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝና አውጣኝ፥ ነፍሴን እንደ አንበሳ ነጥቀው እንዳይሰብሩዋት፥ የሚያድንና የሚታደግ ሳይኖር። አቤቱ አምላኬ፥ እንዲህ አድርጌ ከሆነ፥ ዓመፃም በእጄ ቢኖር፥ መልካም ላደረጉልኝም ክፉን መልሼላቸው ከሆነ፥ ጠላቴንም በከንቱ ገፍቼው ከሆነ፥ ጠላት ነፍሴን ያሳድዳት ያግኛትም፥ ሕይወቴንም በምድር ላይ ይርገጣት፥ ክብሬንም በትቢያ ላይ ያዋርዳት። አቤቱ፥ በመዓትህ ተነሥ፥ በጠላቶቼ ላይ በቁጣ ተነሣባቸው፥ አቤቱ አምላኬ፥ ባዘዝኸው ትእዛዝ ንቃ። የአሕዛብም ጉባኤ ይከብብሃል፥ በእነርሱም ላይ ወደ ከፍታ ተመለስ። ጌታ በሕዝቦች ላይ ይፈርዳል፥ አቤቱ፥ እንደጽድቄ ፍረድልኝ፥ እንደ የዋህነቴም ይሁንልኝ። የክፉዎች በደል ይጥፋ፥ ጻድቁን ግን አቅና፥ እግዚአብሔር ልብንና ኩላሊትን ይመረምራል። ጋሻዬ በእግዚአብሔር ዘንድ ነው ልበ ቅኖችን የሚያድናቸው። እግዚአብሔር ጻድቅ ዳኛ ነው፥ ሁልጊዜ ትክክለኛ ፈራጅ ነው፥ ለማይመለስ ግን ሰይፉን ይስላል፥ ቀስቱን ወጥሮአል አዘጋጅቷልም፥ የሞት መሣርያንም አሰናድቷል፥ ፍላጻዎቹንም የሚንበለበሉ አደረገ። እነሆ፥ ክፋትን ያማጠ ተንኮልን ፀነሰ፥ ውሸትንም ወለደ። ጉድጓድን ማሰ ቈፈረም። በሠራውም ጉድጓድ ይወድቃል። ጉዳቱ በራሱ ይመለሳል፥ ዓመፃውም በአናቱ ላይ ትወርዳለች።