መዝሙር 47:1-9
መዝሙር 47:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ በአምላካችን ከተማ በመቅደሱ ተራራ ምስጋናው ብዙ ነው። ለምድር ሁሉ ደስታን የሚያዝዝ፥ የጽዮን ተራራዎች በመስዕ በኩል ናቸው። የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናት። በተቀበሏት ጊዜ እግዚአብሔር በረከትዋን ያውቃል እነሆ፥ የምድር ነገሥታት ተሰብስበው በአንድነት መጥተዋል። እነርሱስ ይህን አይተው አደነቁ፥ ደነገጡ፥ ፈሩም። መንቀጥቀጥም ያዛቸው፥ እንደ ወላድም በዚያ አማጡ። በኀይለኛ ነፋስ የተርሴስን መርከቦች ትቀጠቅጣቸዋለህ። እንደሰማን እንዲሁ አየን፥ በሠራዊት ጌታ ከተማ፥ በአምላካችን ከተማ፤ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ያጸናታል። አምላክ ሆይ፥ በአሕዛብ መካከል ይቅርታህን ተቀበልን።
መዝሙር 47:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሕዝቦች ሁላችሁ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፤ ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር እልል በሉ። በምድር ሁሉ ላይ ታላቅ የሆነው ንጉሥ፣ ልዑል እግዚአብሔር የሚያስፈራ ነውና። ሕዝቦችን ከእኛ በታች አደረገ፤ መንግሥታትንም ከእግራችን ሥር አስገዛልን። ለሚወድደው ለያዕቆብ ክብር የሆነችውን፣ ርስታችንን እርሱ መረጠልን። ሴላ አምላክ በእልልታ፣ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ። አምላካችንን አወድሱት፤ አወድሱት፤ ንጉሣችንን አወድሱት፤ አወድሱት፤ እግዚአብሔር የምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና፤ ምርጥ ዝማሬ አቅርቡለት። እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ ነግሧል፤ እግዚአብሔር በተቀደሰ ዙፋኑ ላይ ተቀምጧል። ከአብርሃም አምላክ ሕዝብ ጋራ፣ የሕዝቦች መኳንንት ተሰበሰቡ፤ የምድር ነገሥታት የእግዚአብሔር ናቸውና፤ እርሱም እጅግ ከፍ ከፍ ያለ ነው።
መዝሙር 47:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሕዝቦች ሁሉ፥ በደስታ አጨብጭቡ! ከፍ ባለ ድምፅ በመዘመር፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ! በምድር ሁሉ ላይ ታላቁ ገዢ ልዑል እግዚአብሔር ምንኛ አስፈሪ ነው? እርሱ ሕዝቦች ጸጥ ብለው እንዲገዙልንና መንግሥታትም በቊጥጥራችን ሥር እንዲሆኑ አደረገ። ርስት አድርገን የምንይዛትን ምድር መረጠልን፤ ይህችም ምድር ለሚወድደው ለእስራኤል ሕዝብ መመኪያ ናት። እግዚአብሔር በእልልታና በመለከት ድምፅ ዐረገ። ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ! ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ! አምላካችን የዓለም ሁሉ ንጉሥ ነው፤ ስለዚህ የምስጋና መዝሙር ዘምሩለት! እግዚአብሔር በተቀደሰ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦአል፤ መንግሥታትንም የሚያስተዳድር እርሱ ነው። የመንግሥታት መሪዎች ከአብርሃም አምላክ ሕዝብ ጋር ይሰበሰባሉ፤ የምድር ገዢዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ናቸውና፤ እርሱ ከሁሉም በላይ ከፍ ያለ ነው።
መዝሙር 47:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አሕዛብ ሁላችሁ፥ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፥ በደስታ ቃልም ለእግዚአብሔር እልል በሉ። ጌታ ልዑል ግሩምም ነውና፥ በምድር ሁሉ ላይም ታላቅ ንጉሥ ነውና። አሕዛብን ከእኛ በታች፥ ወገኖችንም ከእግራችን በታች አስገዛልን። ለሚወደው ለያዕቆብ ኩራት የሆነችውን ርስታችንን እርሱ ይመርጥልናል። አምላክ በእልልታ፥ ጌታ በመለከት ድምፅ ዐረገ። ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ፥ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ። እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና፥ በጥበብ ዘምሩ። እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ነገሠ፥ እግዚአብሔር በተቀደሰው ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል።