መዝሙር 30:1-12 - Compare All Versions
መዝሙር 30:1-12 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
አቤቱ፥ አንተን ታመንሁ፤ ለዘለዓለምም አልፈር፤ በጽድቅህም አስጥለኝ፥ አድነኝም። ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ፈጥነህም አድነኝ፤ ታድነኝ ዘንድ አምላኬ መድኀኒቴና የመጠጊያዬ ቤት ሁነኝ። ኀይሌና መጠጊያዬ አንተ ነህና ስለ ስምህ ምራኝ፥ መግበኝም፤ አቤቱ፥ አንተ ረዳቴ ነህና ከሰወሩብኝ ከዚች ወጥመድ አውጣኝ። በእጅህ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ፤ የጽድቅ አምላክ እግዚአብሔር፥ ተቤዠኝ። ከንቱን ነገር የሚጠብቀውን ሁሉ ሁልጊዜ ጠላህ፤ እኔ ግን በእግዚአብሔር ታመንሁ። በትድግናህ ደስ ይለኛል፤ ሐሴትም አደርጋለሁ። መከራዬን አይተሃልና፥ ነፍሴንም ከጭንቀት አድነሃታልና። በጠላቴ እጅ አልዘጋኸኝም፥ በሰፊም ስፍራ እግሮቼን አቆምህ። ተቸግሬአለሁና አቤቱ ይቅር በለኝ፥ ዐይኔም ከቍጣ የተነሣ ታወከች፥ ነፍሴም፥ ሆዴም። ሕይወቴ በመከራ አልቋልና፥ ዘመኔም በጩኸት፤ ኀይሌ በችግር ደከመ፥ አጥንቶቼም ሁሉ ተነዋወጡ። በጠላቶቼ ሁሉ ዘንድ ተሰደብሁ፥ ይልቁንም በጎረቤቶቼ ዘንድ፥ ለዘመዶቼም አስፈሪ ሆንሁ፤ በሜዳ ያዩኝም ከእኔ ሸሹ። እንደ ሞተ ሰው ከልብ ረሱኝ፥ እንደ ጠፋ ዕቃም ሆንሁ።
መዝሙር 30:1-12 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ከታች አንሥተኸኛልና፣ ጠላቶቼም በላዬ እንዳይደሰቱ አድርገሃልና፣ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ። እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ትረዳኝ ዘንድ ወደ አንተ ጮኽሁ፤ አንተም ፈወስኸኝ። እግዚአብሔር ሆይ ነፍሴን ከሲኦል አወጣሃት፤ ወደ ጕድጓድ ከመውረድም መልሰህ ሕያው አደረግኸኝ። እናንተ የምትታመኑት፤ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ቅዱስ ስሙንም አወድሱ። ቍጣው ለዐጭር ጊዜ ነው፤ ቸርነቱ ግን እስከ ዕድሜ ልክ ነውና፤ ሌሊቱን በልቅሶ ቢታደርም፣ በማለዳ ደስታ ይመጣል። እኔም በተረጋጋሁ ጊዜ፣ “ከቶ አልናወጥም” አልሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ በአንተ ሞገስ፣ ተራሮቼ ጸኑ፣ ፊትህን በሰወርህ ጊዜ ግን፣ ውስጤ ታወከ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ ተጣራሁ፤ ወደ ጌታም እንዲህ ብዬ ጮኽሁ፤ “በእኔ ወደ ጕድጓድ መውረድ፣ በመሞቴ ምን ጥቅም ይገኛል? ዐፈር ያመሰግንሃልን? ታማኝነትህንስ ይናገራልን? እግዚአብሔር ሆይ፤ ስማ፤ ማረኝም፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ረዳት ሁነኝ።” ዋይታዬን ወደ ሽብሸባ ለወጥህልኝ፤ ማቄን አውልቀህ ፍሥሓን አለበስኸኝ፤ እንግዲህ ነፍሴ ታመስግንህ፤ ዝምም አትበል፤ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ለዘላለም አመሰግንሃለሁ።
መዝሙር 30:1-12 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
አምላክ ሆይ! ስላዳንከኝና ጠላቶቼ በእኔ ላይ እንዲደሰቱ ስላላደረግህ እጅግ አመሰግንሃለሁ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እንድትረዳኝ ወደ አንተ ተጣራሁ፤ አንተም ፈወስከኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ነፍሴን ከሲኦል አወጣሃት፤ ወደ ጥልቁም ከመውረድ ሕይወቴን ጠበቅኸው። ለእርሱ ታማኞች አገልጋዮች የሆናችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን በዝማሬ አመስግኑት! ለቅዱስ ስሙም ምስጋና አቅርቡለት! እርሱ የሚቈጣው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ቸርነቱ ግን ለዘለዓለም ነው፤ ሌሊት ሲለቀስ ዐድሮ በማለዳ ደስታ ይሆናል። ዋስትና እንዳለኝ ስላወቅሁ “ከቶ አልሸነፍም” አልኩ። እግዚአብሔር ሆይ! ሞገስን በሰጠኸኝ ጊዜ እንደማይነቃንቅ ተራራ አበረታኸኝ፤ ፊትህን በሰወርክ ጊዜ ግን ተስፋ ቈረጥኩ። እግዚአብሔር ሆይ! አንተን ጠራሁህ፤ ምሕረትንም ለመንኩህ። እኔ ወደ መቃብር ብወርድ ምን ይጠቅምሃል? ወደ ዐፈርነት ከተለወጥሁ በኋላ እንዴት ላመሰግንህ እችላለሁ? ታማኝነትህንስ እንዴት መናገር ይቻለኛል? እግዚአብሔር ሆይ! ስማኝ፤ ማረኝም፤ እግዚአብሔር ሆይ! እርዳኝ። አንተ ሐዘኔን ወደ ደስታ ለወጥክልኝ፤ ትካዜዬን ከእኔ አስወገድክልኝ፤ የማቅ ልብሴን አውልቀህ ደስታን አለበስከኝ። ስለዚህ ዝም አልልም፤ ለአንተ የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ! አንተ አምላኬ ነህ፤ ስለዚህ ለዘለዓለም አመሰግንሃለሁ።
መዝሙር 30:1-12 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
አቤቱ፥ ተቀብለኸኛልና፥ ጠላቶቼንም ደስ አላሰኘህብኝምና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ። አቤቱ አምላኬ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ አንተም ፈወስከኝ። አቤቱ፥ ነፍሴን ከሲኦል አወጣሃት፥ ወደ ጉድጓድም እንዳልወርድ አዳንኸኝ። ቅዱሳን ሆይ፥ ለጌታ ዘምሩ፥ ለቅድስናውም መታሰቢያ አመስግኑ። ቁጣው ለጥቂት ጊዜ ነው፥ ሞገሱ ግን ለሕይወት ዘመን፥ ልቅሶ ማታ ይመጣል፥ ጥዋት ግን ደስታ ይሆናል። እኔም በደስታዬ፦ ለዘለዓለም አልታወክም አልሁ። አቤቱ፥ በፈቃድህ እንደ ጽኑ ተራራ አጠነከርከኝ፥ ፊትህን ስትሰውር፥ እኔም ደነገጥሁ። አቤቱ፥ ወደ አንተ ጠራሁ፥ ወደ አምላኬም ለመንሁ። ወደ ጉድጓድ ብወርድ ከደሜ ምን ጥቅም ይገኛል? አፈር ያመሰግንሃልን? እውነትህንም ይናገራልን? ጌታ ሰማ ማረኝም፥ ጌታ ረዳቴ ሆነኝ። ልቅሶዬን ወደ እልልታ ለወጥህልኝ፥ ማቄን ቀድደህ ደስታንም አስታጠቅኸኝ።