መዝሙር 2:1-12
መዝሙር 2:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አሕዛብ ለምን ዶለቱ? ወገኖችስ ለምን ከንቱ ይናገራሉ? የምድር ነገሥታት ተነሡ፥ አለቆችም በእግዚአብሔርና በመሲሑ ላይ እንዲህ ሲሉ በአንድነት ተሰበሰቡ። “ማሰሪያቸውን ከእኛ እንበጥስ፥ ቀንበራቸውንም ከእኛ ላይ እንጣል።” በሰማይ የሚኖር እርሱ ይሥቅባቸዋል። እግዚአብሔርም ይሣለቅባቸዋል። በዚያን ጊዜ በቍጣው ይናገራቸዋል፥ በመዓቱም ያውካቸዋል። እኔ ግን በእነርሱ ላይ ንጉሥ ሆኜ ተሾምሁ በተቀደሰ ተራራው በጽዮን ላይ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እናገር ዘንድ፥ እግዚአብሔር አለኝ፥ “አንተ ልጄ ነህ፥ እኔም ዛሬ ወለድሁህ። ለምነኝ፥ አሕዛብን ለርስትህ የምድርንም ዳርቻ፥ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ። በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ፥ እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃም ትቀጠቅጣቸዋለህ።” አሁንም እናንት ነገሥታት፥ ልብ አድርጉ፤ እናንት የምድር ፈራጆችም፥ ተገሠጹ። ለእግዚአብሔር በፍርሀት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ። ጥበብን አጽኑአት፤ እግዚአብሔር እንዳይቈጣ፥ እናንተም ከጽድቅ መንገድ እንዳትጠፉ፥ ቍጣው ፈጥና በነደደች ጊዜ፥ በእርሱ የታመኑ ሁሉ ብፁዓን ናቸው።
መዝሙር 2:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አሕዛብ ለምን በቍጣ ተነሣሡ? ሕዝቡስ ለምን በከንቱ አሤሩ? የምድር ነገሥታት ተነሡ፤ ገዦችም በእግዚአብሔርና በመሲሑ ላይ ሊመክሩ ተሰበሰቡ፤ “ሰንሰለታቸውን እንበጥስ፣ የእግር ብረታቸውንም አውልቀን እንጣል” አሉ። በሰማይ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ይሥቃል፤ ጌታም ይሣለቅባቸዋል። ከዚያም በቍጣው ይናገራቸዋል፤ በመዓቱም ያስደነግጣቸዋል፤ ደግሞም፣ “እኔ ግን በተቀደሰው ተራራዬ፣ በጽዮን ላይ የራሴን ንጉሥ ሾምሁ” ይላል። የእግዚአብሔርን ሕግ ዐውጃለሁ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤ ለምነኝ፤ መንግሥታትን ርስት አድርጌ፣ የምድርንም ዳርቻ ግዛት እንዲሆንህ እሰጥሃለሁ። አንተም በብረት በትር ትቀጠቅጣቸዋለህ፤ እንደ ሸክላ ዕቃ ታደቅቃቸዋለህ።” ስለዚህ እናንተ ነገሥታት ልብ በሉ፤ እናንተ የምድር ገዦችም፣ ተጠንቀቁ። እግዚአብሔርን በፍርሀት አገልግሉት፤ ለርሱ በመንቀጥቀጥ ደስ ያሰኛችሁ። እንዳይቈጣና በመንገድ እንዳትጠፉ፣ ዝቅ ብላችሁ ልጁን ሳሙት፤ ቍጣው ፈጥኖ ይነድዳልና። እርሱን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ ብፁዓን ናቸው።
መዝሙር 2:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አሕዛብ ስለምን ያሤራሉ? ሕዝቦችስ ለምን በከንቱ ያድማሉ? እግዚአብሔርንና መሲሑን ለመቃወም የዓለም ነገሥታት ተነሣሡ፤ ሹሞቻቸውም ከእነርሱ ጋር ተባበሩ። “እግር ብረታቸውን ከእግራችን እንቊረጥ፤ ገመዳቸውን በጥሰን እንጣል” አሉ። በሰማይ ዙፋኑ ላይ የሚቀመጠው ይስቅባቸዋል፤ በከንቱ ሐሳባቸውም ጌታ ያፌዝባቸዋል። ከዚህ በኋላ በቊጣው ይገሥጻቸዋል፤ በመዓቱም ያስፈራራቸዋል። “በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ ንጉሤን ሾምኩ” ይላቸዋል። “የእግዚአብሔርን ዐዋጅ ዐውጃለሁ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድኩህ፤ ለምነኝ፤ አሕዛብ ሁሉ እንዲገዙልህ አደርጋለሁ፤ ምድርም በሙሉ የአንተ ርስት ትሆናለች። በብረት በትር ትሰብራቸዋለህ፤ እንደ ሸክላ ዕቃም ቀጥቅጠህ ታደቃቸዋለህ’ ” አለኝ። እናንተ ነገሥታት አስተውሉ፤ እናንተ የምድር ገዢዎች ተጠንቀቁ። እግዚአብሔርን በፍርሃት አገልግሉት፤ በመንቀጥቀጥም ተገዙለት። ቊጣው በቅጽበት ስለሚነድ በእናንተ ላይ ተቈጥቶ እንዳያጠፋችሁ በመንቀጥቀጥ ስገዱለት እርሱን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ የተባረኩ ናቸው።
መዝሙር 2:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አሕዛብ ለምን ያጉረመርማሉ? ለምንስ ከንቱዉን ያሰላስላሉ? የምድር ነገሥታት ተነሡ፥ አለቆችም በጌታና በመሢሑ ላይ ተማከሩ፦ ማሰርያቸውን እንበጥስ፥ ገመዳቸውንም ከእኛ እንጣል። በሰማያት የሚቀመጠውም እርሱ ይሥቃል፥ ጌታም ይሣለቅባቸዋል። በዚያን ጊዜ በቁጣው ይናገራቸዋል፥ በመዓቱም ያውካቸዋል። እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ። ትእዛዙን እናገራለሁ፥ ጌታ አለኝ፦ “አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ።” ለምነኝ፥ አሕዛብን ለርስትህ የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ። በብረት በትር ትቀጠቅጣቸዋለህ፥ እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃም ታደቃቸዋለህ። አሁንም እናንት ነገሥታት፥ ልብ አድርጉ፥ እናንት የምድር ፈራጆችም፥ ተገሠጹ። ለጌታ በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ። ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቈጣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ፥ ቁጣው ፈጥና ትነድዳለችና። በእርሱ የታመኑ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው።