መዝሙር 18:16-24
መዝሙር 18:16-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከላይ እጁን ዘርግቶ ያዘኝ፤ ከጥልቅ ውሆችም ውስጥ አወጣኝ፤ ከብርቱ ጠላቶቼ አዳነኝ፤ ከሚበረቱብኝ ባላጋሮቼም ታደገኝ። እነርሱ በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ድጋፍ ሆነኝ። ወደ ሰፊ ስፍራ አወጣኝ፤ ደስ ተሰኝቶብኛልና አዳነኝ። እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መለሰልኝ፤ እንደ እጄም ንጽሕና ከፈለኝ፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፤ አምላኬንም በመተው ክፉ አላደረግሁም። ሕጎቹ ሁሉ በፊቴ ናቸው፤ ከሥርዐቱም ዘወር አላልሁም። በፊቱ ነቀፋ አልነበረብኝም፤ ራሴንም ከኀጢአት ጠብቄአለሁ። እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መጠን፣ በፊቱ እንደ እጄም ንጽሕና ከፈለኝ።
መዝሙር 18:16-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ከላይ ሆኖ እጁን በመዘርጋት ያዘኝ፤ ከጥልቅ ውሃም ስቦ አወጣኝ። በጣም በርትተውብኝ ከነበሩት ከኀይለኞች ጠላቶቼና ከሚጠሉኝ ሰዎች ሁሉ እጅ እግዚአብሔር አዳነኝ። እኔ በተቸገርኩበት ጊዜ በጠላትነት ተነሡብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ጠበቀኝ። ወደ ሰፊ ቦታ አወጣኝ፤ በእኔ ደስ ስለ ተሰኘም አዳነኝ። እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤ እንደ እጄም ንጽሕና ይመልስልኛል። እኔ የእግዚአብሔርን መንገድ ተከትዬአለሁ፤ ፊቴን ከአምላኬ በመመለስ ክፉ ነገር አላደረግሁም። የእግዚአብሔርን ሕጎች ሁሉ እፈጽማለሁ ሥርዓቱንም ከማክበር ወደ ኋላ አላልኩም። በእርሱ ዘንድ ንጹሕ ነበርኩ፤ ከኃጢአትም ራሴን ጠብቄአለሁ። እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ፥ እንደ እጄም ንጽሕና፥ ዋጋዬን ከፈለኝ።
መዝሙር 18:16-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ከዘለፋህ ከአፍንጫህ እስትንፋስ የተነሣ፥ የውኆች ምንጮች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ። ከላይ ሰደደ ወሰደኝም፥ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ። ከብርቱዎች ጠላቶቼ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፥ በርትተውብኝ ነበርና። በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፥ ጌታ ግን ድጋፍ ሆነኝ። ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፥ ወድዶኛልና አዳነኝ። ጌታ እንደጽድቄ ይከፍለኛል፥ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል። የጌታን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁም። ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፥ ሥርዓቱንም ከፊቴ አላራቅሁም። በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ።