መዝሙር 18:1-6
መዝሙር 18:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል። ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፥ ሌሊትም ለሌሊት ጥበብን ትናገራለች። ቃላቸው ያልተሰማበት ነገር የለም፥ መናገርም የለም፥ ቃላቸው ወደ ምድር ሁሉ ወጣ። ነገራቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ደረሰ። በፀሐይ ውስጥ ድንኳኑን አደረገ፥ እርሱም እንደ ሙሽራ ከእልፍኙ ይወጣል፤ በመንገዱ እንደሚራመድ አርበኛ ደስ ይለዋል። አወጣጡ ከሰማያት ዳርቻ ነው፥ መግቢያውም እስከ ዓለም ዳርቻ ነው፤ ከትኩሳቱም የሚሰወር የለም።
መዝሙር 18:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጕልበቴ እግዚአብሔር ሆይ፤ እወድድሃለሁ። እግዚአብሔር ዐለቴ፣ መጠጊያዬና ታዳጊዬ ነው፤ አምላኬ የምሸሸግበት ዐለቴ፤ እርሱ ጋሻዬ፣ የድነቴ ቀንድና ዐምባዬ ነው። ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ። የሞት ገመድ ዐነቀኝ፤ ምናምንቴ ነገርም አጥለቀለቀኝ። የሲኦል ገመድ ተጠመጠመብኝ፤ የሞት ወጥመድም ተጋረጠብኝ። በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እንዲረዳኝም ወደ አምላኬ ጮኽሁ፤ እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ ጩኸቴም በፊቱ ከጆሮው ደረሰ።
መዝሙር 18:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! ኀይል የምትሰጠኝ አንተ ስለ ሆንክ፥ እወድሃለሁ። እግዚአብሔር አለቴ፥ አምባዬና አዳኜ ነው፤ አምላኬ የምጠጋበት አለቴ ነው፤ እርሱ ጋሻዬና የመዳኔ ቀን፥ ጠንካራ መመኪያም ነው። ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ እርሱም ከጠላቶቼ ያድነኛል። የሞት ጣር ከበበኝ፤ የጥፋት ጐርፍም አጥለቀለቀኝ። የሲኦል ገመድ ተበተበኝ፤ የሞት ወጥመድም ተጠመደብኝ። መከራ በደረሰብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እንዲረዳኝም አምላኬን ለመንኩት፤ በመቅደሱ ሆኖ ድምፄን ሰማ፤ ጩኸቴንም አደመጠ።