መዝሙር 146:3-9
መዝሙር 146:3-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ልባቸው የቈሰለውን ይፈውሳል፥ ቍስላቸውንም ያደርቅላቸዋል። ከዋክብትንም በሙሉ ይቈጥራቸዋል፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል። እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ ኀይሉም ታላቅ ነው፥ ለጥበቡም ቍጥር የለውም። እግዚአብሔር የዋሃንን ያነሣቸዋል፥ ኃጥአንን ግን እስከ ምድር ድረስ ያዋርዳቸዋል። ለእግዚአብሔር በምስጋና ዘምሩ፥ ለአምላካችንም በመሰንቆ ዘምሩ፤ ሰማዩን በደመናት የሚሸፍን፥ ለምድርም ዝናምን የሚያዘጋጅ፥ ሣርን በተራሮች ላይ፥ ልምላሜውንም ለሰው ልጆች አገልግሎት የሚያበቅል፥ ለእንስሶችና ለሚጠሩት ለቍራዎች ጫጩቶች፥ ምግባቸውን የሚሰጣቸው እርሱ ነው።
መዝሙር 146:3-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችም አትመኩ። መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል። ብፁዕ ነው፤ ረዳቱ የያዕቆብ አምላክ የሆነ፣ ተስፋውንም በአምላኩ በእግዚአብሔር ላይ የጣለ ሰው፤ እርሱ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ የፈጠረ፣ ታማኝነቱም ለዘላለም የሆነ ነው፤ ለተበደሉት የሚፈርድ፣ ለተራቡት ምግብን የሚሰጥ እርሱ ነው፤ እግዚአብሔር እስረኞችን ከእስራት ያወጣል፤ እግዚአብሔር የዕውራንን ዐይን ያበራል፤ እግዚአብሔር የተዋረዱትን ከፍ ያደርጋል፤ እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ ድኻ አደጎችንና መበለቶችን ይደግፋል፤ የክፉዎችን መንገድ ግን ያጠፋል።
መዝሙር 146:3-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ማዳን ስለማይችሉ በመሪዎች ወይም በማንኛውም ፍጡር አትተማመኑ። እነርሱ በሚሞቱበት ጊዜ ወደ ዐፈር ይመለሳሉ፤ በዚያኑ ቀን ዕቅዳቸው ሁሉ ይጠፋል። የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነለትና በአምላኩ በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረገ ሰው ደስ ይበለው፤ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ሁሉ የፈጠረ ነው። እርሱ ዘወትር ቃል ኪዳኑን ይጠብቃል፤ ለተጨቈኑት ፍትሕን ይሰጣል፤ ለተራቡ ምግብን ይሰጣል። እስረኞችን ነጻ ያወጣል። የዕውሮችን ዐይን ያበራል፤ የወደቁትን ያነሣል፤ ጻድቃንን ይወዳል። እግዚአብሔር መጻተኞችን ይጠብቃል፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆች ይረዳል፤ የክፉዎችን ዕቅድ ግን ያፈርሣል።
መዝሙር 146:3-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ማዳን በማይችሉ በአለቆች፥ በሰው ልጅ፥ አትታመኑ። ነፍሱ ትወጣለች ወደ መሬቱም ይመለሳል፥ ያንጊዜ እቅዶቹ በሙሉ ይጠፋሉ። የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ ተስፋውም በጌታ በአምላኩ የሆነ ሰው ምስጉን ነው፥ እርሱም ሰማይንና ምድርን ባሕርንም፥ በእነርሱ ያለውንም ሁሉ የፈጠረ፥ እውነትን ለዘለዓለም የሚጠብቅ፥ ለተበደሉት የሚፈርድ፥ ለተራቡ ምግብን የሚሰጥ ነው። ጌታ የታሰሩትን ይፈታል፥ ጌታ የዕውሮችን ዐይን ያበራል፥ ጌታ የወደቁትን ያነሣል፥ ጌታ ጻድቃንን ይወድዳል፥ ጌታ ስደተኞችን ይጠብቃል፥ ወላጆች የሞቱባቸውንና ባልቴቶችን ይቀበላል፥ የክፉዎችንም መንገድ ያጠፋል።