መዝሙር 144:2-8
መዝሙር 144:2-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በየቀኑ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም ለዘለዓለም ዓለም ምስጋና አቀርባለሁ። እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ ምስጋናውም እጅግ ብዙ ነው፤ ለታላቅነቱም ዳርቻ የለውም። የልጅ ልጆች ሥራህን ያደንቃሉ፥ ኀይልህንም ይናገራሉ፥ የቅድስናህንም ክብር ታላቅነት ይናገራሉ፥ ተአምራትህንም ያስረዳሉ። “ኀይልህ ግሩም ነው” ይላሉ፥ ግርማህንም ይነጋገራሉ፥ ብርታትህንም ያስረዳሉ። የቸርነትህን ብዛት መታሰቢያ ይናገራሉ፥ በጽድቅህም ሐሤትን ያደርጋሉ። እግዚአብሔር ይቅር ባይና መሓሪ ነው፥ መዐቱ የራቀ፥ ምሕረቱ የበዛ እውነተኛ ነው፤
መዝሙር 144:2-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እርሱ አፍቃሪ አምላኬና ጽኑ ዐምባዬ ነው፤ ምሽጌና ታዳጊዬ፣ የምከለልበትም ጋሻዬ ነው፤ ሕዝቤን የሚያስገዛልኝም እርሱ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን ያህል በልብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ታስበውስ ዘንድ የሰው ልጅ እስከዚህ ምንድን ነው? ሰው እንደ እስትንፋስ ነው፤ ዘመኑም ፈጥኖ እንደሚያልፍ ጥላ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰማያትህን ሰንጥቀህ ውረድ፤ ይጤሱም ዘንድ ተራሮችን ዳስስ። የመብረቅ ብልጭታ ልከህ በትናቸው፤ ፍላጻህን ሰድደህ ግራ አጋባቸው። እጅህን ከላይ ዘርጋ፤ ከኀይለኛ ውሃ፣ ከባዕዳንም እጅ ታደገኝ፤ አድነኝም። አንደበታቸው ሐሰትን ይናገራል፤ ቀኝ እጃቸውም የቅጥፈት ቀኝ እጅ ናት።
መዝሙር 144:2-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ጠባቂዬና መከታዬ ነው፤ መጠለያዬና አዳኜ ነው፤ በእርሱ ተማምኜ በሰላም እኖራለሁ፤ እርሱ አሕዛብን ከእግሬ በታች አድርጎ ያስገዛልኛል። እግዚአብሔር ሆይ! ይህን ያኽል የምትንከባከበው ሰው ምንድን ነው? ይህን ያኽልስ የምታስብለት የሰው ልጅ ምንድን ነው? ሰው እንደ ነፋስ ሽውታ ነው፤ ዘመኑም እንደ ጥላ የሚያልፍ ነው። እግዚአብሔር ሆይ! ሰማይን ሰንጥቀህ ውረድ፤ ተራራዎችን ዳስስ፤ እነርሱም ይጢሱ። የመብረቅ ብልጭታን ልከህ ጠላቶችህን በትናቸው፤ ፍላጻዎችህንም በመወርወር አሳዳቸው። እጅህን ከላይ ስደድ፤ ከጥልቅ ውሃ ውስጥ ስበህ አውጣኝ፤ ታደገኝም፤ ከባዕዳን ኀይል አድነኝ። እነርሱ ከቶ እውነት አይናገሩም፤ ቀኝ እጃቸውን አንሥተው የሚምሉት በሐሰት ነው።
መዝሙር 144:2-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
መሓሪዬና መሸሸጊያዬ፥ መጠጊያዬና መድኃኒቴ፥ ረዳቴና መታመኛዬም፥ ሕዝቤንም ከእኔ በታች የሚያስገዛልኝ። አቤቱ፥ እርሱን ታውቀው ዘንድ ሰው ምንድነው? ታስብለት ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው? ሰው ከንቱን ነገር ይመስላል፥ ዘመኑ እንደ ጥላ ያልፋል። አቤቱ፥ ሰማዮችህን ዝቅ ዝቅ አድርጋቸው ውረድም፥ ተራሮችን ዳስሳቸው ይጢሱም። መብረቆችህን ብልጭ አድርጋቸው በትናቸውም፥ ፍላጾችህን ላካቸው አስደንግጣቸውም። እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም ከብዙ ውኆች፥ አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር፥ ቀኛቸው የሐሰት ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ።