መዝሙር 140:1-13

መዝሙር 140:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር ሆይ፤ ከክፉ ሰዎች አድነኝ፤ ከዐመፀኞችም ሰዎች ጠብቀኝ፤ እነርሱ በልባቸው ክፉ ነገር ያውጠነጥናሉ፤ በየዕለቱም ጦርነት ይጭራሉ። ምላሳቸውን እንደ እባብ ያሾላሉ፤ ከከንፈራቸውም በታች የእፉኝት መርዝ አለ። ሴላ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከክፉዎች እጅ ጠብቀኝ፤ እግሮቼንም ለመጥለፍ ከሚያደቡ ዐመፀኞች ሰውረኝ። ትዕቢተኞች ወጥመድ በስውር አስቀመጡብኝ፤ የመረባቸውን ገመድ ዘረጉብኝ፤ በመንገዴም ላይ አሽክላ አኖሩ። ሴላ እግዚአብሔር ሆይ፤ “አንተ አምላኬ ነህ” እልሃለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የልመና ጩኸቴን ስማ። ብርቱ አዳኝ የሆንህ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ በጦርነት ዕለት የራስ ቍር ሆንኸኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ የክፉዎች ምኞት አይፈጸም፤ በትዕቢትም እንዳይኵራሩ፣ ዕቅዳቸው አይሳካ። ሴላ ዙሪያዬን የከበቡኝ ሰዎች ራስ፣ የከንፈራቸው መዘዝ ይጠምጠምበት። የእሳት ፍም በላያቸው ይውረድ፤ ዳግመኛም እንዳይነሡ ወደ እሳት ይጣሉ፤ ማጥ ወዳለበት ጕድጓድ ይውደቁ። ምላሰኛ በምድሪቱ ጸንቶ አይኑር፤ ዐመፀኛውን ሰው ክፋት አሳድዶ ያጥፋው። እግዚአብሔር ለድኻ ፍትሕን እንደሚያስከብር፣ ለችግረኛውም ትክክለኛ ፍርድን እንደሚሰጥ ዐውቃለሁ። ጻድቃን በእውነት ስምህን ያመሰግናሉ፤ ቅኖችም በፊትህ ይኖራሉ።

መዝሙር 140:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር ሆይ! ከክፉ ሰዎች አድነኝ፤ ከዐመፀኞች እጅም ጠብቀኝ። የእነርሱ ልብ ክፉ ዕቅዶችን ያቅዳል፤ ዘወትርም ጥልን ያነሣሣሉ። ምላሳቸው እንደ መርዛም እባብ ተናዳፊ ነው፤ ቃላቸውም እንደ እፉኝት መርዝ ነው። እግዚአብሔር ሆይ! ከክፉዎች ኀይል ጠብቀኝ፤ እኔን ለመጣል ከሚያቅዱ ከዐመፀኞች ሰዎች ጠብቀኝ። ትምክሕተኞች ወጥመድ ዘረጉብኝ፥ እንደ መረብ የተጠላለፈ ገመድም ዘረጉብኝ። እኔንም ለመያዝ በመንገዴ ላይ ወጥመድ አጠመዱ። እግዚአብሔርን “አንተ አምላኬ ነህ” እለዋለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ! ምሕረትህን ለማግኘት ስጸልይ ስማኝ! ኀያሉ አዳኜ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ! በጦርነት ቀን ራሴን እንደ ጋሻ ሸፍንልኝ። ለክፉዎች የሚፈልጉትን ነገር አትስጣቸው፤ ዕቅዳቸው እንዲሰምር አታድርግ። የከበቡኝ ጠላቶቼ በእኔ ላይ ያቀዱትን ሤራ በእነርሱ ላይ እንዲፈጸም አድርግ። የእሳት ፍም በላያቸው ይውደቅ፤ ወደ ጒድጓድም ይጣሉ፤ ከዚያም ከቶ አይውጡ። ሌሎችን በሐሰት የሚከስሱ በምድር ላይ ጸንተው አይኑሩ፤ ክፉ ነገር በጨካኞች ሰዎች ላይ ይድረስ፤ ይደምስሳቸውም። እግዚአብሔር ሆይ! ለድኾች እንደምትፈርድ፥ ለተጨቈኑትም መብታቸውን እንደምታስከብር ዐውቃለሁ። ደጋግ ሰዎች በእውነት ያመሰግኑሃል፤ በፊትህም ጸንተው ይኖራሉ።

መዝሙር 140:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አቤቱ፥ ከክፉ ሰው አድነኝ፥ ከዓመፀኞች ሰዎች ጠብቀኝ በልባቸውም ክፉ ካሰቡ፥ ቀኑን ሁሉ ለሰልፍ ከሚከማቹ። ምላሳቸውን እንደ እባብ ሳሉ፥ ከከንፈራቸው በታች የእፉኝት መርዝ አለ። አቤቱ፥ ከክፉዎች እጅ ጠብቀኝ፥ እርምጃዬንም ሊያሰናክሉ ከመከሩ ከዓመፀኞች አድነኝ። ትዕቢተኞች ወጥመድን ሰወሩብኝ፥ ለእግሮቼም የወጥመድ ገመድን ዘረጉ፥ በመንገድ ዕንቅፋትን አኖሩ። ጌታንም፦ አንተ አምላኬ ነህ፥ የልመናዬን ቃል፥ አቤቱ፥ አድምጥ አልሁት። አቤቱ፥ ጌታዬ፥ የመድኃኒቴ ጉልበት፥ በሰልፍ ቀን ራሴን ሸፈንህ። አቤቱ፥ ከምኞቴ የተነሣ ለክፉዎች አትስጠኝ፥ ተንኮላቸው እንዲሳካ አትፍቀድ። የሚከብቡኝ ራሳቸውን አነሡ፥ የከንፈራቸው ክፋት ይክደናቸው። የእሳት ፍም በላያቸው ይውደቅ፥ እንዳይነሡም ወደ እሳትና ወደ አዘቅት ይጣሉ። ተናጋሪ ሰው በምድር ውስጥ አይጸናም፥ ዓመፀኛን ሰው ክፋት ለጥፋት ይፈልገዋል። ጌታ ለድሀ ዳኝነትን ለችግረኛም ፍርድን እንደሚያደርግ አወቅሁ።